የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ2017 የጋቦን አፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ከሌሶቶ ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ ዝግጅቱን ትላንት ጀምሯል፡፡
ዋልያዎቹ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌን አሰናብተው ገብረመድህን ሃይሌ እና ረዳቶቹ ውብሸት ደሳለኝ እና ዘላለም ሽፈራውን ከሾሙ በኋላ የ25 ተጨዋቾች ምርጫ አከናውነው ሰኞ ኢንተርኮትኔንታል አዲስ ማረፊያቸውን በማድረግ ትላንት ልምምዳቸውን ጀምረዋል፡፡
በዛሬ ጠዋት የልምምድ ፕሮግራም ለቅዱስ ጊዮርጊስ እና አል ሂላል የወዳጅነት ጨዋታ ወደ ሱዳን ካመሩት ሳላዲን ሰኢድ ፣ ምንተስኖት አዳነ ፣ በሃይሉ አሰፋ ፣ አስቻለው ታመነ እንዲሁም የፕሪቶርያ ዩኒቨርሲቲው ጌታነህ ከበደ እና የፔትሮጄቱ ሽመልስ በቀለ በቀር ቀሪዎቹ 19 ተጫዋቾች ተገኝተዋል፡፡ የማላቀቅ ፣ በፈጣን እንቅስቃሴ ውስጥ ኳስ የመቀባበል እንዲሁም በግማሽ ሜዳ ለሁለት ተከፍለው መጫወትም የዛሬ ልምምዳቸው አካል ነበር፡፡
የዋልያዎቹ ልምምድ በቀጣዮቹ ቀናት ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን ከዛሬ ጀምሮ ለተወሰኑ ቀናት በቀን ሁለት ጊዜ ልምምድ የሚሰሩ ይሆናል፡፡
ከቡድኑ ጋር ያልተካተቱት አምስት ተጨዋቾች በዚህ ሳምንት መጨረሻ ከቡድኑ ጋር የሚቀላቀሉ ሲሆን ፕሪቶርያ ዩኒቨርሲቲ እሁድ ላለበት ወሳኝ የመውረድ/መትረፍ ትንቅንቅ ጌታነህ ከበደን የሚጠቀም በመሆኑ ቶሎ እንደማይለቀው ለኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ደብዳቤ የላከ በመሆኑ ሰኞ አአ በመግባት ማክሰኞ ልምምድ የሚጀምር ይሆናል፡፡
ብሄራዊ ቡድናችን በመጪው ግንቦት 28 ከሌሶቶ ብሄራዊ ቡድን ጋር የምድቡን 5ኛ ጨዋታ በማሴሩ ከተማ ያደርጋል፡፡