ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአል ሂላል ያለግብ አቻ ተለያይቷል

በኦምዱሩማን ሂላል ስታዲየም በተደረገ የወዳጅነት ጨዋታ የኢትዮጵያ ፕሪምየርሊግ መሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሱዳን ፕሪምየርሊግ መሪ አል ሂላል ጋር ያለግብ አቻ ተለያይቷል፡፡

የሁለቱ ሃገራትን ግንኙነትን ለማጠንከር በተደረገው የወዳጅነት ፍልሚያው ጨዋታ አላስፈላጊ ጉሽሚያዎች በጨዋታው ላይ ታይቷል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ በ10 ተጫዋቾች የጨረሱት ፈረሰኞቹ ግባቸውን ባለማስደፈር ከሂላል ጋር 0-0 ሊለያዩ ችለዋል፡፡

በጨዋታው መጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ የጨዋታ ብልጫ የነበራቸው ባለሜዳዎቹ በተደጋጋሚ የጊዮርጊስ የግብ ክልል መድረስ ቢችሉም በ2ኛው ደቂቃ የተደረገውን ሙከራ ሮበርት ኦዶንካራ ካመከነው በኀላ ሌላ የግብ ሙከራ ለማድረግ ረጅም ደቂቃዎችን መጠበቅ አስፈልጓቸው ነበር፡፡

በ32ኛው ደቂቃ በ2015 በካፍ የአፍሪካ ምርጥ 10 ሽልማት ውስጥ ገብቶ የነበረው ሙዳትሂር ካሬካ ከኦዶንካራ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ኳስ እና መረብን ማገናኘት የሚችልበትን ዕድል አምክኗል፡፡

ፈረሰኞቹ በሂደት ወደ እየተሻሻሉ ቢመጡም የግብ ሙከራ በማድረግ ግን ስኬታማ አልነበሩም፡፡

በአመዛኙ ለፊት አጥቂው ሳላዲን ሰዒድ ኳስ የመጣል ስትራቴጂን የተጠቀሙት ፈረሰኞቹ በተደጋጋሚ የሂላል ተከላካይ ክፍልን ሰብረው መግባት ሲቸግራቸው ታይቷል፡፡ የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሶስት ደቂቃዎች ሲቀሩት አዳነ ግርማ ፈረሰኞቹ መሪ መሆን የሚችሉበትን ዕድል ቢያገኘም ኳስን በግቡ አናት ሰዷታል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ የግብ ጠባቂ ለውጥ ያደረጉት ጊዮርጊሶች በሂላል ተፈትነዋል፡፡ በ55ኛው ደቂቃ ኤድዋርድ ሳዶምባ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ ሳይጠቀምበት የቀረ ሲሆን ከሁለት ደቂቃዎች በኃላ የዕለቱ ሱዳናዊው አርቢትር አዳነን በቀይ ካርድ አስወጥተውታል፡፡ በዳኛው ውሳኔ ደስተኛ ያልተነበረው አዳነ አርቢትሩ ጋር እሰጣገባ ውስጥ ሲገባም ተስተውሏል፡፡

ሂላሎች ከቀይ ካርዱ በኃላ የነበራቸውን የቁጥር ብልጫ መጠቀም ሳይችሉ ጨዋታው 0-0 በሆነ ውጤት ተፈፅሟል፡፡

ፈረሰኞቹ የሱዳን ቆይታቸውን አጠናቅቀው ነገ ወደ አዲስ አበባ የሚመለሱ ሲሆን በጨዋታው ላይ ሙሉ 90 ደቂቃ የተጫወተው አጥቂው ሳላዲን ሰዒድ፣ አስቻለው ታመነ፣ በኃይሉ አሰፋ እና ምንተስኖት አዳነ ዋልያዎቹን የሚቀላቀሉ ይሆናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *