የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የዋልያዎቹን ስራ በጊዜያዊነት ከተረኩ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ አሰልጣኙ በጋዜጣዊ መግለጫው ካነሷቸው ነጥቦች መካከል በዝግጅት ፣ በብሄራዊ ቡድናችን የማለፍ ተስፋ እና የወዳጅነት ጨዋታ ዙርያ የተናገሩትን አቅርበንላችኋል፡፡
ስለ ዝግጅቱ
‹‹ ዝግጅቱ በጥሩ ሁኔታ አልፏልማለት ይቻላል፡፡ ከቅዱስ ጊዮጊስ ጋር ወደ ሱዳን ያመሩት እና ከውጪ ክለቦች ከመጡት ተጫዋቾች በቀር አብዛኛዎቹ በጊዜ ተሰባስበው ዝግጅታቸውን አከናውነዋል፡፡ ››
‹‹ በዝግጅት ወቅት ተጫዋቾች ያሳዩት ተነሳሽነት እና ፍላጎት በአጠቃላይ በጣም ጥሩ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ከዛም ውጪ ፌዴሬሽኑ ብዙ ነገር ለማገዝ ጥረት አድርጓል፡፡ ››
‹‹ ነገ ወደ ሌሶቶ የምንበረው ጠዋት በመሆኑ እና ቀኑን ሙሉ ጉዞ የምናደርግ በመሆኑ ነገን እንደ እረፍት እንጠቀምበታለን፡፡ ሀሙስ ሌሶቶ ላይ ልምምድ እናደርጋለን፡፡ ››
የማለፍ እድል
‹‹ የቡድናችን የማለፍ እድል በሌሎች ምድቦች ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ በየምድቡ 2ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ከኛ የተሸለ ነጥብ አላቸው፡፡ በአሁኑ ሰአት ያለን ተስፋ አሸንፈን በሌሎች ምድቦች የሚገኙ ቡድኖችን ውጤት መጠባበቅ ስለሆነ እድላችንን ለመጠቀም የቻልነውን ያህል እንጥራለን፡፡ ስለዚህ በማጥቃት ላይ የተመሰረተ ጨዋታ ይዘን እንቀርባለን፡፡ ነገር ግን የመከላከሉንም ሒደት አንዘነጋውም፡፡ ››
‹‹ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተአምር እንፈጥራለን ባንልም የስፖርት ቤተሰቡ ስሜት እንዲመለስ ጥረት ለማድረግ ተዘጋጅተናል፡፡ ››
የወዳጅነት ጨዋታ
‹‹ በዝግጅት ፕላን ውስጥ የወዳጅነት ጨዋታ አቅርቤ የነበረ ቢሆንም ባለመገኘቱ ለምን ብዬ አላስቸገርኩም፡፡ ፌዴሬሽኑ ሞክሯል ፤ ግን አልተሳካም፡፡ ››
‹‹ የዛሬው የወዳጅነት ጨዋታ ብዙ ነገር ያሳየናል ብለን አናስብም፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ተጫዋቾች ከልምምድ ባሻገር በጨዋታ ላይ ምን ሊያሳዩ እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጥቶናል፡፡ ››