ጋቦን 2017 – የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ዛሬ ይቀጥላሉ

የ2017 የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ሲደረጉ የማይበገሩት አናብስት ወደ ጋቦን የሚወስዳቸውን ትኬት ለመቁረጥ ይጫወታሉ፡፡

ከምድብ አንድ ሶስት ሃገራት ወደ አፍሪካው ዋንጫው ለማለፍ የተሻለ ይዘዋል፡፡ ላይቤሪያ፣ ቶጎ እና ቱኒዚያ ምድቡን በበላይነት ለመጨረስ ሲፋጠጡ ለሃገራቱ ነጥብ እና ግብ በማደል ላይ የምትገኘው ጅቡቲ የምድቡን ግርጌ ይዛለች፡፡

ቱኒዚያ ዛሬ ጅቡቲን ከሜዳዋ ውጪ ትገጥማለች፡፡ በምድብ ማጣሪያው በከፍተኛ የግብ ልዩነት የተጠናቀቀው ጨዋታ ቱኒዝ ላይ በነዚሁ ሃገራት መካከል የተካሄደው ሲሆን ቱኒዚያ ጅቡቲን 8-1 መርታት ችላለች፡፡ በቱኒዚያዊው አሰልጣኝ ኑረዲን ጋርሳሊ የምትመራው ጅቡቲ ያለምንም ነጥብ የምድቡ ግርጌ ላይ ትገኛለች፡፡ ቱኒዚያ የማለፍ ተስፋዋን ለማለምለም ጠንካራ ቡድን ይዛ የምትቀርብ ሲሆን እንደ ፈረጃኒ ሳሲ፣ አሊ ማሎል እና ዋህቢ ካዘሪን ያካተት ስብስብ ወደ ጅቡቲ አቅንቷል፡፡ ምደቡን ላይቤሪያ በዘጠኝ ነጥብ ስትመራ የካርቴጅ ንስሮቹ በሰባት ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል፡፡

ካሜሮን ከምድብ 13 ለማለፍ ሞሪታንያን ከሜዳዋ ውጪ ናውኩቾ ላይ ማሸነፍ ይጠበቅባታል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለች የመጣችው ሞሪታንያ ከማይበገሩት አንበሶች በአንድ ነጥብ ብቻ አንሳ ሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧ ጨዋታውን እንዲጠበቅ አድርጎታል፡፡ ካሜሮን በመጀመሪያው ጨዋታ በቪንሰንት አቡበከር ብቸኛ ግብ ሞሪታንያን የረታች ሲሆን የፊት መስመር ተሰላፊዎቿ አቡበከር እና ኤሪክ ማክሲም ቺፖ ሞቲንግ ለስ ሞርቢቶንስ ፈተና ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በፈረንሳዊው አሰልጣኝ ኮረንቲን ማርቲን ስር እየሰለጠነ የሚገኘው የሞሪታንያ ብሄራዊ ቡድን ናውክቾ ላይ ለተጋጣሚ ቡድኖች ፈተና እየሆነ የመጣ ሲሆን በምድብ ማጣሪያው እስካሁን አንድም ጨዋታ በሜዳው አልተሸነፈም፡፡ በፈረንሳይ ሊግ 2 በመጫወት ላይ የሚገኘው የሞሪታንያ ብሄራዊ ቡድን አማካይ ጉይድሌይ ዲያሎ ወደ ናውክቾ ባለመምጣቱ ጨዋታው የሚያመልጠው ይሆናል፡፡

ከምድብ 6 ቀድማ ማለፏን ያረጋገጠችው ሞሮኮ ቱኒዝ ላይ ከወዲሁ የማለፍ ተስፋዋ የጨለመውን ሊቢያን ትገጥማለች፡፡ ሄርቬ ሬናርድ የአሰልጣኝነት መንበሩን ከያዘ ጀምሮ የተሳካ የማጣሪያ ጉዞ ማድረግ የቻሉት የአትላስ አምበሶቹ ሊቢያን የማሸነፍ ቅድመ ግምት በሰፊው አግኝተዋል፡፡ ሊቢያ ለጥሩ ሁለተኝነት ለመፎካከር የግድ የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ ቢኖርባትም ሊቢያ ውስጥ ባለው ያለመረጋጋት ምክንያት በገለልተኛ ሜዳ መደረጉ ከባድ ያደርግባታል፡፡

 

የዛሬ ጨዋታዎች፡

15፡30 – ጅቡቲ ከ ቱኒዚያ (ስታደ ናሽናል ኤል ሃጂ ሃሰን ጉሌድ አፕቲዶን)

17፡00 – ሞሪታንያ ከ ካሜሮን (ኦፊስ ዱ ኮምፕሌክስ ኦሎምፒክ ደ ናውኩቾ)

19፡00 – ሊቢያ ከ ሞሮኮ (ስታደ ኦሎምፒክ ደ ራደስ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *