ጋቦን ለምታስተናግደው አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ሶስተኛ ቀኑን ዛሬ የሚይዘው የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች በተለያዩ የአፍሪካ ከተሞች ቀጥለው ይደረጋሉ፡፡ ዛሬ 11 ጨዋታዎች ሲደረጉ ታንዛኒያ ግብፅን ቦትስዋና ደግሞ ዩጋንዳን የሚያስተናግዱበት ጨዋታ ከፍተኛ ትኩረት ስቧል፡፡
የቻድ እግርኳስ ፌድሬሽን ባለበት የፋይናንስ ቀውስ ምክንያት ከአፍሪካ ዋንጫው የምድብ ማጣሪያ ራሱን ማግለሉን ተከትሎ ሶስት ሃገራት ብቻ በምድብ ሰባት ይገኛሉ፡፡ ለአፍሪካ ዋንጫው ከ2010 በኃላ ዳግም ለመጀመሪያ ጊዜ ለማለፍ የተቃረበችው ግብፅ ለማለፍ ሁለት ጨዋታዎችን የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ የገባችው ታንዛኒያን ዳሬ ሰላም ላይ ትገጥማለች፡፡ ፈርኦኖቹ የምድብ ማጣሪያው የመጨረሻው ጨዋታቸው ሲሆን የታይፋ ከዋክብቶቹ የዛሬውን ጨምሮ ሁለት ቀሪ ጨዋታዎች አላቸው፡፡ ከዚሁ ምድብ ናይጄሪያ አስቀድማ መውደቋን አረጋግጣለች፡፡ የግብፅ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሄክቶር ኩፐር በመሃመድ ሳላ ላይ ከፍተኛ እምነት ሲጥሉ ታንዛኒያዎች በማቡዋና ሳማታ ፣ ቶማስ ኡሌሙንጉ እና በኤልያስ ማጉሊ የተገነባው የአጥቂ መስመራቸው የፈርኦኖቹን የተከላካይ ክፍል ይፈትናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ምድቡን ግብፅ በሰባት ነጥብ ስትመራ ናይጄሪያ እና ታንዛኒያ ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡ ታንዛኒያ በአቋም መለኪያ ጨዋታ ከሜዳዋ ውጪ ኬንያን ቀጥማ 1-1 ተለያይታለች፡፡
ተመሳሳይ ዜና | ካሜሮን ወደ ጋቦን 2017 የአፍሪካ ዋንጫ ማምራቷን አረጋግጣለች
በምድብ አራት ፍራንሲስታውን ላይ ቦትስዋና ዩጋንዳን ታስተናግዳለች፡፡ በእርስ በርስ ግንኙነት በቡርኪናፋሶ ተበልጣ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ያላችው ዩጋንዳ በአንድ ነጥብ ብቻ ከምታንሰው ቦትስዋና ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ከፍተኛ ግምትን አግኝቷል፡፡ ክሬንሶቹ ከ1978 ወዲህ ወደ ለአህጉሪቱ ታላቅ ውድድር አልፈው የማያውቁ ሲሆን በተደጋጋሚም ለማለፍ ከጫፍ ደርሰው ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡ ዜብራዎቹ በአቋም መለኪያ ጨዋታ የኢትዮጵያን ተጋጣሚ ሌሶቶን 2-1 ማሸነፍ የቻሉ ሲሆን ዩጋንዳ በዚምባቡዌ 2-0 ተረትታለች፡፡
የ2015 ሻምፒዮኗ ኮትዲቯር አዘጋጇን ጋቦንን አቢጃን ላይ ታስተናግዳለች፡፡ የጋቦን የምድብ ጨዋታዎቹን እንደወዳጅነት ጨዋታ ምልከታ ቢኖራቸውም ምድቡን ከመምራት ግን አላገዳትም፡፡ ምድብ ዘጠኝን በሰባት ነጥብ የምትመራው ጋቦን ከአፍሪካ ሻምፒዮኖቹ ከባድ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ጋቦን በአቋም መለኪያ ጨዋታ ስፔን ላይ በሞሪታንያ 2-0 ተሸንፋች፡፡ ኮትዲቯር የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ለማረጋገጥ የግድ ጨዋታውን ማሸነፍ አለባት፡፡ በምድብ ሌላኛው ጨዋታ ሴራሌዮን ከሱዳን ይለማሉ፡፡ በሂሳብ ስሌት አሁንም ተስፋቸው ያልተማጠጠው ሁለቱ ሃገራት ከጋቦን በሶስት ነጥብ አንስው ሶስተኛ እና አራተኛ ናቸው፡፡ የጋቦን ትኬቷን ለመቅረት ከጫፍ የደረሰችው ሴኔጋል ቡጁምቡራ ላይ ቡሩንዲን ትገጥማለች፡፡
ምድብ 11ላይ በ12 ነጥብ የሚመሩት የታራንጋ አንበሶቹ የ100% የማሸነፍ ሪከርዳቸውን ለማስቀጠል ቡሩንዲ ደግሞ ለጥሩ ሁለተኝነት የሚያበቃትን ውጤትን ለማግኘት ወደ ሜዳ ይገባሉ፡፡ ማሊ ጁባ ላይ ደቡብ ሱዳንን ማሸነፍ ከቻለች ለአፍሪካ ዋንጫው ማለፏን ታረጋግጣለች፡፡
በምድብ ሶስት ከማሊ በሁለት ነጥብ ብቻ አንሳ ሁለተኛ የምትገኘው ቤኒን በፊፋ ብትታገድም ካፍ ቤኒን ከኢኳቶሪያል ጊኒ የሚያደርጉት ጨዋታ ይሰረዛ አይሰረዝ የላው ነገር የለም፡፡ ቢቢሲ ስፖርት በዘገባው ካፍን ጠቅሶ ባወጣው መረጃ መሰረት ካፍ ከፊፋ የቤኒን መታገድ ካላነሳ ቤኒን ከማጣሪያው ትሰረዛለች፡፡ የቤኒን ቅጣት ከፀና ማሊ የማለፍ ተስፋዋን ታለመልማለች፡፡ ከቤኒን ጋር የተያዙ ነጥቦች በሙሉም ተቀናሽ ይሆናሉ፡፡ ቤኒን በአንፃሩ ለጥሩ ሁለተኝነት ከሚፎካከሩ ሃገራት ጥሩ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡
በምደብ አምስት ቢሳው ላይ ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ለመቃረብ የ2012 አሸናፊዋ ዛምቢያ ከጊኒ ቢሳው ይፋጠጣሉ፡፡ በመጋቢት ወር በተካሄዱት የማጣሪያ ጨዋታዎች ኬንያን ማሸነፏን ተከትሎ ከምድቡ ግርጌ ወደ መሪነት ሳይጠበቅ የመጣችው ጊኒ ቢሳው በሜዳዋ በጠንካራ አቋም ላይ መገኘቷ ጨዋታውን ለዛምቢያ ያከብደዋል ተብሏል፡፡ ዛምቢያ በሳምንቱ አጋማሽ ባደረገቻቸው ሁለት የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች በቶጎ ስትሸነፍ ከጋምቢያ ጋር 1-1 ወጥታለች፡፡ የደቡብ አፍሪካ አብሳ ፕሪምየርሺፕ የ2015/16 የውድድር ዘመን ኮከብ ግብ አግቢ ኮሊንስ ሙቤዙማ፣ ሬንፎርድ ካላባ እና ናታን ሲንካላ የመሳሰሉ ከዋክብቶችን የያዙት ቺፖሎፖሎዎቹ ጊኒ ቢሳውን መርታት ለአፍሪካ ዋንጫው መግቢያ በር ያቀርባቸዋል፡፡
ባኩ ላይ ጋምቢያ ከደቡብ አፍሪካ ይጫወታሉ፡፡ ካሜሮን ከምድብ 13 ወደ አፍሪካ ዋንጫው ማለፏን ተከትሎ ከመርሃ ግብር ማሙያነት ባለፈ ሁለቱ ሃገራት ወደ አፍሪካ ዋንጫው የማለፋቸው ነገር አክትሟል፡፡
የዛሬ ጨዋታዎች፡
15፡00 – ቡሩንዲ ከ ሴኔጋል (ፕሪንስ ሉዊ ሩዋጋሶሬ)
15፡30 – ሩዋንዳ ከ ሞዛምቢክ (አማሆሮ ስታዲየም)
15፡30 ሳኦ ቶሜ እና ፕሪንስፔ ከ ኬፕ ቨርድ (ስታዲዪ 12 ጁላይ)
16፡00 – ጊኒ ቢሳው ከ ዛምቢያ (ስታዲዮ 24 ስፕቴምበር)
16፡00 – ታንዛኒያ ከ ግብፅ (ናሽናል ስታዲየም)
16፡00 – ናሚቢያ ከ ኒጀር (ሳም ኑጆማ ስታዲየም)
16፡00 – ቦትስዋና ከ ዩጋንዳ (ፍራንሲስታወን ስታዲየም)
16፡30 – ሴራሌዮን ከ ሱዳን (ሲአካ ስቲቨንስ ስታዲየም)
16፡30 – ደቡብ ሱዳን ከ ማሊ (ጁባ ስታዲየም)
17፡00 – ጋምቢያ ከ ደቡብ አፍሪካ (ባኩ ስታዲየም)
17፡30 – ኮትዲቯር ከ ጋቦን (ስታደ ደ ቦአኬ)