ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ፡ ደደቢት የዞኑ ቻምፒዮን መሆኑን አረጋገጠ

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ መካከለኛ-ሰሜን ዞን 21ኛ ሳምንት ዛሬ በተደረጉ ጨዋታዎች ሲጀምሩ ደደቢት ሁለት ጨዋታ እየቀረው የዞኑ ቻምፒዮን መሆኑን አረጋግጧል፡፡

10:00 ላይ ኤሌክትሪክን የገጠሙት ደደቢቶች በሁለተኛው አጋማሽ ባስቆጠሯቸው ግቦች ታግዘው 5-2 አሸንፈዋል፡፡ ኤሌክትሪክ አማረች ገረመው በፍፁም ቅጣት ምት ባስቆጠረችው ግብ የመጀመርያው አጋማሽን 1-0 በመምራት ቢያጠናቅቁም ደደቢት በሁለተኛው አጋማሽ ሎዛ አበራ (2) ፣ መስከረም ካንኮ ፣ ትበይን መስፍን እና የኤሌክትሪክ ተከላካይ በራሷ ግብ ላይ ባስቆጠሯቸው ግቦች 5-1 መምራት ችለዋል፡፡ ኤሌክትሪኮች በዮርዳኖስ ፍስህ አማካኝነት ድንቅ ግብ ቢያስቆጥሩም ከሽንፈት መዳን አልቻሉም፡፡

PicsArt_1465061334903

ድሉን ተከትሎ ከ18 ጨዋታ 51 ነጥቦች የሰበሰበው ደደቢት የመካከለኛው-ሰሜን ዞን ቻምፒዮን መሆኑን ሲያረጋግጥ ኤሌክትሪክ ወደ ማጠቃለያ ውድድሩ ማለፋቸውን ለማረጋገጥ ተጨማሪ ጨዋታ ለመጠበቅ ተገደዋል፡፡

ደደቢት በውድድር ዘመኑ ከ1 ሽንፈት በቀር ሁሉንም ጨዋታዎች በድል ያጠናቀቀ ሲሆን በሁሉም ጨዋታዎች ላይ ግብ ያስቆጠረችው እና በ42 ግቦች የከፍተኛ ግብ አግቢነቱን የምትመራው ሎዛ አበራ ለደደቢት ያማረ የውድድር ዘመን የጎላ ሚና ተጫውታለች፡፡

PicsArt_1465061422225

በ08:00 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ልደታ ክ/ከተማን ገጥሞ 6-0 አሸንፏል፡፡ የንግድ ባንክን የድል ግቦች ብዙሃን እንዳለ (2) ፣ ሽታዬ ሲሳይ ፣ ብዙነሽ ሲሳይ (2) እና እፀገነት ብዙነህ ከመረብ አሳርፈዋል፡፡

የዞኑ ውድድር ሊጠናቀቅ የ22ኛ ሳምንት እና ሳይደረግ የተዘለለው የ18ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ብቻ የቀሩ ሲሆን ደደቢት ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ መከላከያ ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ዳሽን ቢራ ሀዋሳ ለሚካሄደው የማጠቃለያ ውድድር ማለፋቸውን ሲያረጋግጡ ኤሌክትሪክ ለማለፍ ከቀሪዎቹ 3 ጨዋታዎች 1 ነጥብ ብቻ ይበቃዋል፡፡

ከደቡብ-ምስራቅ ዞን ቻምፒዮኑ ሀዋሳ ከተማ ፣ ሲዳማ ቡና ፣ ድሬዳዋ ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ ከሰኔ 13-30 በሀዋሳ ለሚካሄደው የማጠቃለያ ውድድር ያለፉ ክለቦች ናቸው፡፡

PicsArt_1465061553798


ውጤቶች ፣ ቀጣይ ጨዋታዎች እና ሰንጠረዥ

ቅዳሜ ግንቦት 27 ቀን 2008

ልደታ ክ/ከተማ 0-6 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ብዙነሽ ሲሳይ (2) ፣ ብዙሃን እንዳለ (2) ፣ ሽታዬ ሲሳይ ፣ እፀገነት ብዙነህ

ደደቢት 5-2 ኢትዮ ኤሌክትሪክ
ሎዛ አበራ (2) ፣ መስከረም ካንኮ ፣ ትበይን መስፍን ፣ ቤተልሄም ከፍያለው (በራሷ ግብ ላይ) | አማረች ገረመው (ፍቅም) ፣ ዮርዳኖስ ፍስሃ

እሁድ ግንቦት 28 ቀን 2008

08፡00 ሙገር ሲሚንቶ ከ ቅድስት ማርያም ዩኒቨርሰቲ (አአ ስታድየም)

09፡00 ዳሽን ቢራ ከ መከላከያ (ጎንደር)

10፡00 ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ኢትዮጵያ ቡና (አአ ስታድየም)

PicsArt_1465061274828

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *