ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታ ሌሶቶ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዛሬ በሚጫወትበት ሰአትና ሜዳ የመጨረሻ ልምምዱን ሰርቷል፡፡
ረቡዕ ጠዋት ከአዲስ አበባ ተነስተው አመሻሹን ማሴሩ የደረሱት ዋልያዎቹ ከሃሙስ ጀምሮ ልምምድ ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን ዛሬ ቀለል ያለ ልምምድ ሰርተዋል፡፡ በቡድኑ ምንም የተጫዋች ጉዳት እንደሌለ የታወቀ ሲሆን ዘግይቶ ሊቀላቀል እንደሚችል ሲጠበቅ የነበረው ስዩም ተስፋዬ ጉዳይ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ በነገው ጨዋታ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ቆይታ የቡድኑ አባላት በጥሩ ተነሳሽነት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
” ሁሌም ልምምድ ከመግባታችን በፊት የተወሰነ ደቂቃ እንነጋገራለን፡፡ ሁሉም በጥሩ መንፈስና ተነሳሽነት ላይ ይገኛሉ ፤ የሚሰጣቸውን ተቀብለውም ይተገብራሉ፡፡ ነገም በሚገባ ሜዳው ላይ እንደሚያሳዩት አስባለው፡፡ ከጉዳት ጋር ያጋጠመን ምንም ችግር የለም ፤ ሁሉም በሙሉ ጤንነት ላይ ይገኛሉ ” ብለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን በተጨዋችነት እና ረዳት አሰልጣኝነት የምናውቃቸው ገብረመድህን ኃይሌ የዋሊያዎቹ ዋና አሰልጣኝነት ስራቸውን በድል ለመጀመር ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
“የመጀመርያ ጨዋታዬን በድል ለመወጣት ፍላጎቱ አለኝ፡፡ ማሸነፍ እፈልጋለው ፤ ተጫዋቾችም ጋር ይህ ፍላጎት አለ፡፡
የተጋጣሚያችን አሁን ያሉበትን ወቅታዊ ብቃት ምን ላይ እንዳለ ባናቅም ጥሩ ነገር እሰራለን ፤ እኔም ይህን አሳካለው “ሲሉ አክለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከሌሶቶ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ነገ 10:00 ላይ በሴሴቶ ስታድየም ይደረጋል፡፡