የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ጨዋታዎች ብዙ ግብ የተቆጠረባቸው ሆነው አልፈዋል፡፡ ግብፅ እና ሴኔጋል የምስራቅ አፍሪካ ተጋጣሚዎቻቸውን በማሸነፍ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ሲያልፉ ዩጋንዳ እና ጊኒ ቢሳው ወሳኝ የሆነ ድል አስመዝግበዋል፡፡ ሱዳን በሴራሊዮን ተሸንፋ ከአፍሪካ ዋንጫው መቅረቷን አረጋግጣለች፡፡
ፈርኦኖቹ ምድብ ሰባትን በበላይነት መጨረሳቸውን ባረጋገጡበት ጨዋታ የታይፋ ከዋክብቶቹን 2-0 አሸንፈዋል፡፡ ታንዛኒያ የማለፍ ተስፋዋን ለማለምለም ግብፅን 4-0 ከዚያ በላይ ማሸነፍ ቢያስፈልጋቸውም ውጤቱ ተገላቢጦሽ ሆኗል፡፡ አማካዩ መሃመድ ሳላ ሁለቱንም ግቦች በማስቆጠር አሁንም ለግብፅ ወሳኝነቱን አሳይቷል፡፡ ማቡዋና ሳማታ በጨዋታው ላይ የፍፁም ቅጣት ምት አምክኗል፡፡ በጨዋታውን ላይ የ43 ዓመቱ ግብ ጠባቂ ኤሳም ኤል ሃድሪ ከ19 ወራት ቆይታ በኃላ ለመጀመሪያ ግዜ ለብሄራዊ ቡድኑ በቋሚነት ተሰልፏል፡፡
የሪከርድ ሰባት ግዜ የአፍሪካ ሻምፒዮኗ ግብፅ ከ2010 በኃላ ለመጀመሪያ ገዜ በአርጀንቲናዊው ዕውቅ ታክቲሽያን ሄክቶር ኩፐር እየተመራች ወደነገሰችበት አፍሪካ ዋንጫ ማለፍ ችላለች፡፡
ዩጋንዳ ቦትስዋናን ፋራንሲስታውን ላይ 2-1 በማሸነፍ ከ1978 በኃላ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ዕድሏን አስፍታለች፡፡ ሉዋጋ ኪዚቶ እና ካሊድ ኦቾ የክሬንሶቹን የድል ግቦች አስቆጥረዋል፡፡ ለዜብራዎቹ ኦንካቤትስ ማክጋንታይ ብቸኛዋን ግብ በስሙ አስመዝግቧል፡፡ ምድብ አራትን በሰርቢያዊው ሰርዮቪች ሚሉቲን ሚቾ የሚሰለጥኑት ዩጋንዳዎች በ10 ነጥብ ሲመሩ ከኮሞሮስ ጋር ዕሁድ የምትጫወተው ቡርኪናፋሶ በሰባት ነጥብ ትከተላለች፡፡ ቦትስዋና ከአፍሪካ ዋንጫው ውጪ መሆኗን አረጋግጣለች፡፡
ተመሳሳይ ዜና | የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን ዛሬ የመጨረሻ ልምምዱን ሰርቷል
ጊኒ ቢሳው በእግርኳስ ታሪኳ ለመጀመሪያ ግዜ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎዋን ለማረጋገጥ የሰፋ ዕድል ይዛለች፡፡ በመጋቢት ወር ከነበሩት ሁለት የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች በፊት በምድብ አምስት ግርጌን ይዘው የነበሩት ጊኒ ቢሳዎች ከሶስት ጨዋታዎች በኃላ በአስደናቂ መልኩ የምድቡ መሪ ለመሆን በቅተዋል፡፡ ቢሳው ላይ ዛምቢያን ያስተናገዱት ባለሜዳዎቹ 3-2 አሸንፈዋል፡፡ ሆዜ ሉዊዝ ሜንዴስ ሎፔዝ (ዚዚንሆ) ቢሳውን በፍፁም ቅጣት ምት ግብ ቀዳሚ ሲያደርግ ኮሊንስ ሙቤዙማ ቺፖሎፖሎዎቹን አቻ አድርጓል፡፡ አርኖድ ሜንዲ ቢሳውን መሪነት ሲመልስ የ2012 የቢቢሲ የአፍሪካ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ክርስቶፈር ካቶንጎ በግንባሩ በመግጨት ዛምቢያን ዳግም አቻ አድርጓል፡፡ በጭማሪ ሰዓት ቶኒ ሲልቫ የጊኒ ቢሳውን የድል ግብ አስቆጥሯል፡፡ በምድቡ ሌላ ጨዋታ ኬንያ ኮንጎ ብራዛቪልን ማሸነፍ ከቻለች ጊኒ ቢሳው ለመጀመሪያ ጊዜ ለአፍሪካ ዋንጫ ታልፋለች፡፡ ምድቡን ጊኒ ቢሳው በ10 ነጥብ ስትመራ ኮንጎ እና ዛምቢያ በዕኩል ስድስት ነጥብ ተከታዩቹን ደረጃ ይዘዋል፡፡
ጁባ ላይ ደቡብ ሱዳን ሽንፈትን ቀምሳለች፡፡ በምድብ ሶስት ጨዋታ ማሊን ያስተናገደችው የአህጉሪቱ አዲስ ሃገር ደቡብ ሱዳን 3-0 ተሸንፋለች፡፡ የማሊን የድል ግቦች አብዱላሂ ዲያቢ፣ ሞቢዶ ማይጋ እና ሙሳ ዶምቢያ በስማቸው አስመዝግበዋል፡፡ የደቡብ ሱዳኑ ጄምስ ጆሴፍ የማሊው አምበል ሲላ ያኮባን በክር በመማታቱ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል፡፡ ማሊ ምድብን በ13 ነጥብ እየመራች ሲሆን ፊፋ የቤኒን እግርኳስ ፌድሬሽን የምርጫ ጠቅላላ ጉባኤውን እስከ ሰኔ 4 ማድረግ ከቻለ በሚቀጥለው ቀን እሁድ ሰኔ ኤኳቶሪያል ጊኒን የምትገጥም ይሆናል፡፡ ጠቅላላ ጉባኤው ካልተልካሄደ ቤኒን ከአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ትሰረዛለች፡፡
ተመሳሳይ ዜና | ካሜሮን ወደ ጋቦን 2017 የአፍሪካ ዋንጫ ማምራቷን አረጋግጣለች
የሰይዶ ማኔ እና ማሜ ቤራም ዲዩፍ የመጀመሪያ አጋማሽ ግቦች የሴኔጋልን የጋቦን 2017 ተሳትፎ ትኬት ቆርጠዋል፡፡ የታራንጋ አንበሶቹ ቡሩንዲን ሜዳዋ ቡጁምቡራ ላይ 2-0 ሲረቱ በማጣሪያው አምስቱንም ጨዋታዎች ያሸነፉ ብቸኛ ብሄራዊ ቡድንም ሆነዋል፡፡ በምድብ 11 ሌላ ጨዋታ ናሚቢያ በፒተር ሳሉሊሌ ግብ አሸንፋለች፡፡ የቡሩንዲ ጎረቤት ሩዋንዳ ኪጋሊ ለይ በሞዛምቢክ 3-2 ተሸንፋለች፡፡ ለሞዛምቢክ ዶሚንጌዝ፣ አፕሰን ማንጅት፣ ሄልደር ፓሌምቤ ሲያስቆጥሩ አማቩቢዎቹን ከመሸነፍ ያላዳኑ ሁለት ግቦች ለኬንያው ጎር ማሂያ ድንቅ ብቃቱን በማሳየት ላይ የሚገኘው ጃኩዌስ ቱሴንግ ከመረብ አዋህዷል፡፡
ሱዳን በሴራሊዮን 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት ተሸንፋ ከአፍሪካ ዋንጫው ውጪ ሆናለች፡፡ የአፍሪካ ሻምፒዮኗ ኮትዲቯር ጋቦንን በጆናታን ኮድያ እና ኢስማኤል ዲዮማንዴ ግቦች 2-1 በማሸነፍ የምድብ 9 መሪነትን ከአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅዋ ተቀብለዋል፡፡ የጋቦንን ግብ የአል አሃሊው አጥቂ ማሊክ ኤቮና አስቆጥሯል፡፡ ደቡብ አፍሪካ ባኩ ላይ ጋምቢያን ታማሳንካ ጋቡዛ እና ኪጋን ዶሊ ግቦች 4-0 ረምርመዋል፡፡
ተመሳሳይ ዜና | አልጄሪያ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፏን አረጋግጣለች
የቅዳሜ ውጤቶች፡
ታንዛኒያ 0-2 ግብፅ
ጊኒ ቢሳው 3-2 ዛምቢያ
ቡሩንዲ 0-2 ሴኔጋል
ሴራሊዮን 1-0 ሱዳን
ደቡብ ሱዳን 0-3 ማሊ
ቦትስዋና 1-2 ዩጋንዳ
ናሚቢያ 1-0 ኒጀር
ሩዋንዳ 2-3 ሞዛምቢክ
ጋምቢያ 0-4 ደቡብ አፍሪካ
ሳአ ቶሜ እና ፕሪንስፔ 1-2 ኬፕ ቬርድ
ኮትዲቯር 2-1 ጋቦን
የዕሁድ ጨዋታዎች፡
14፡00 – ላይቤሪያ ከ ቶጎ (አንቶኔት ቱብማን ስታዲየም)
14፡30 – ማዳጋስካር ከ ዲ.ሪ. ኮንጎ (ስታደ ራቢማናጃራ)
15፡00 – ስዋዚላንስ ከ ጊኒ (ሎባምባ ስታዲየም)
15፡00 – ኮሞሮስ ከ ቡርኪናፋሶ (ስታደ ደ ሞሮኒ)
15፡00 – ኬንያ ከ ኮንጎ ብራዛቪል (ሚስክ ካሳራኒ ስታዲየም)
15፡00 – ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ከ አንጎላ (ኮምፕሌክስ ስፖርቲፍ ባርተለማይ ቦጋንዳ)
15፡00 – ሞሪሸስ ከ ጋና (ስታደ ደ ቤሌ ቩ)
15፡00 – ሌሶቶ ከ ኢትዮጵያ (ሴትሶቶ ስታዲየም)
15፡00 – ዚምባቡዌ ከ ማላዊ (ናሽናል ስፖርትስ ስታዲየም)