ጌታነህ ከበደ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የፊት መስመር የመምራት ሃላፊነትን ባለፉት ተከታታይ ጨዋታዎች ለብቻው በሚያስብል መልኩ በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡ ባለፉት 5 ጨዋታዎችም 7 ግቦች በማስቆጠር ድንቅ አጥቂነቱን አስመስክሯል፡፡
ጌታነህ ባለፈው እሁድ ኢትዮጵያ ሌሶቶን 2-1 ስታሸንፍ ሁለቱንም ግቦች ያሳረፈው ጌታነህ በብሄራዊ ቡድኑ እና ክለቡ ዙርያ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረገውን ቆይታ እንዲህ አቅርበነዋል፡፡
ደደቢትን በአምበልነት መርተህ የፕሪሚየር ሊግ ቻምፒዮን ሆነሃል ፤ አሁን ደግሞ ዋልያዎችን በአምበልነት መርተሃል፡፡ ሃላፊነቱን በንፅፅር እንዴት አየኸው?
” የክለብና የብሄራዊ ቡድን እግርኳስ ትልቅ ልዩነት አለው፡፡ ብሄራዊ ቡድን አምበል ስትሆን የሚሰማህ ስሜት ከፍተኛ ነው ፤ ያለብህም ሀላፊነት ብዙ ነው፡፡ በእርግጥ ክለብ ላይ የነበረኝ አስተዋፅኦ ለብሔራዊ ቡድን በአምበልነት መመረጥ አስተዋፆ አድርጓል”
ዋልያዎቹን በጊዜያዊነት የተረከቡት አሰልጣኝ ገብረመድህን እንዴት አገኘሃቸው?
” ከአሰልጣኝ ገብረመድህን ጋር በደደቢትም አብረን ሰርተናል፡፡ በደንብ እንተዋወቃለን ፤ ጥሩ አሰልጣኝ ነው ፤ ከልጆቹም ጋር ጥሩ መቀራረብና መግባባት አለው፡፡ ”
ከቅርብ ወራት ወዲህ በብሄራዊ ቡድኑ የአጥቂዎች በጉዳት መሳሳት በመፈጠሩ ጎል የማስቆጠሩ ሃላፊነት አንተ ጫንቃ ላይ ሆኗል፡፡ የቡድኑ የጎል ምንጭም አንተ ሆነሃል፡፡ ይህ ሃላፊነት የፈጠረው ተነሳሽነት ነው ?
” ሀላፊነቱ እንዳለ ቢሆንም ዋናው ቁምነገር ጠንክረህ ካልሰራህ እንደዚህ አይነት ውጤት አታመጣም፡፡ ስለሆነም ሁሌም ጠንክሬ በመስራቴ የመጣ ውጤት ነው”
ብሄራዊ ቡድኑ በአልጄርያ (አአ ላይ) እና ሌሶቶ ጨዋታ ላይ ብሄራዊ ቡድኑ ጠፍቶበት የነበረው ተነሳሽነት እና ፍላጎት ያንሰራራ መስሏል፡፡ ህዝቡ ወደሚናፍቀው ውጤታማነት የምንመለስበትን መንገድ መልሰን እያገኘን ብለህ ታስባለህ?
” አሁን ላይ ብሄራዊ ቡድኑ ጥሩ ነው፡፡ የተወሰነ ጊዜያት ላይ ብሄራዊ ቡድኑ ጥሩ ስሜት ውስጥ አልነበረም፡፡ አሁን ላይ ስታየው ተጫዋቾቹ ላይ ጥሩ ስሜት አለ፡፡ ከዚህ ቀደም አመራረጡ ላይ የነበረ ክፍተት ያለ ይመስለኛል ፤ አሁን ላይ በአመራረጥ ላይ ችግር ያለ አይመስለኝም፡፡ ሌላው ቀጣይነት እንዲኖረው ቡድኑ ብዙ ጊዜ አብሮ መቆየት አለበት፡፡ ያ በውጤቱ ቀጣይነት ላይ አስተዋፆ አለው ብዬ አስባለው”
የብሄራዊ ቡድን ፕሮፋይልህ ከሌሎቹ የአፍሪካ አጥቂዎች የማይተናነስ እንዳውም የላቀ ነው ። ነገር ግን በርካታ ክለቦች ለማስፈረም የሚያሳዩት ፍላጎት እምብዛም ነው፡፡ ለምን ይሆን? ኢትዮዽያውያን ላይ ያላቸው ግምት አናሳ ነው ወይስ ሌላ ?
” ያው እሱ ነው፡፡ አንደኛ ደረጃ ለምሳሌ ከአንድ ናይጄርዊ ወይም ካሜሮናዊ ጋር ወደ አንድ ክለብ አብረን ብንሄድ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ለናጄርያዊው ወይም ለካሜሮናዊው ነው፡፡ ይህ ሃገራችን በእግር ኳስ ያላት ስም አነስተኛ መሆኑ ነው እንጂ በብቃት ከእኛ የተሻሉ ሆነው አይደለም ”
በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከፍተኛ ግብ አሰቆጣሪዎች ተርታ ትገኘለህ፡፡ የክረምቱ የዝውውር መስኮት እንደመከፈቱ ወደ ተሻለ ክለብ ለማምራትያለው አስተዋፅኦ ምን ያህል ነው ?
” አዎ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው፡፡ ጎል ማስቆጠርህ ብቻ ሳይሆን በአለም አቀፍ ቻናሎች በሚተላለፍበት ወቅት በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ጎል ስታስቆጥር ያንተ የመታየት እድል ይሰፋል ፤ ፈላጊዎችህም ይጨምራሉ፡፡ ያ ጥሩ ነገሩ ነው፡፡ ”
ከክለብህ ፕሪቶርያ ዩኒቨርሲቲ ጋር በሊጉ ለመቆየት ትግል ላይ ናችሁ…
” አዎ አደጋ ውስጥ ነን፡፡ ቀሪ ሦስት ጨዋታዎች አሉን፡፡ እነዚህን ጨዋታዎች ማሸነፍ ብቻ ነው የሚጠበቅብን፡፡ ይህን ካሳካን በሊጉ የምንቆይ ይሆናል ፤ ይህ ካልሆነ ከባድ ነው የሚሆነው ”
ቀጣይ ቆይታህስ?
” ዘንድሮ ኮንትራቴ ያልቃል፡፡ ወደ የት እንደማመራ እስካሁን አልወሰንኩም፡፡ እዛው በምገኝበት ሀገር ደቡብ አፍሪካ ክለቦች ጥያቄ አቅርበውልኛል፡፡ የት እንደሆነ ማረፊያዬ ወደ ፊት አብረን የምናየው ይሆናል፡፡ “