የኦሬንጅ ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የምድብ ጨዋታዎች ሁለተኛ መርሃ ግብር ዛሬ በሚደረግ አንድ ጨዋታ ይጀመራል፡፡ በምድብ አንድ የስምንት ግዜ የአፍሪካ ሻምፒዮኑ አል አሃሊ የኮትዲቯሩ አሴክ ሚሞሳስን አሌክሳንደሪያ ላይ ይገጥማል፡፡
በምድብ መክፈቻ ጨዋታ ሽንፈትን የቀመሱት ሁለቱም ክለቦች ወደ ግማሽ ፍፃሜው ለማለፍ የሚያደርጉትን ጥረት መስመር ለማስያዝ ይጫወታሉ፡፡ አል አሃሊ ባሳለፍነው ሳምንት ኢስማኤሊን 2-1 በመርታት የግብፅ ፕሪምየር ሊግ ክብርን ዳግም ያገኘ ሲሆን ከዜስኮ ዩናይትድ ሽንፈት በቶሎ ለማገገም የግድ አሴክን ማሸነፍ ይጠበቅበታል፡፡
ቀያዮቹ ሰይጣኖች የፊት መስመራቸው በጉዳት የሳሳ በመሆኑ አሰልጣኝ ማርቲን ዮል አሁንም በጋናዊው ጆን አንቲው ላይ ጥገኛ ይሆናሉ፡፡ በተለያዩ የአውሮፓ ክለቦች እየተፈለገ የሚገኘው የመስመር አማካዩ ረመዳን ሶብሂ በጉዳት ከአሃሊ ስብስብ ውጪ መሆን ሌላው የዮል ጭንቀት ነው፡፡
የአሴክ ሚሞሳስ በሜዳው እና ደጋፊው ፊት በዋይዳድ ካዛብላንካ የተሸነፈ ሲሆን አል አሃሊን ከሜዳው ውጪ የማሸነፍ ተስፋው እምብዛም ነው ተብሏል፡፡
ከአሃሊ በባሰ የሳሳ የአጥቂ መስመር ያለው አሴክ ወደ አሌክሳንደሪያ ያቀናው በአዲስ አበባ ትራንዚት አድርጎ ነው፡፡ ያኒክ ዛክሪያ በአሴክ ሚሞሳስ በኩል የሚጠበቅ ተጫዋች ነው፡፡
የሁለቱ ክለቦችን ጨዋታ ለመታደም 15ሺህ ደጋፊዎች ፍቃድ እንዳገኙ የግብፅ እግርኳስ ድህረገፅ ኪንግፉት ዘግቧል፡፡
የአንደኛ ዙር መርሃ ግብር ውጤቶች
ዜስኮ ዩናይትድ (ዛምቢያ) 3-2 አል አሃሊ (ግብፅ)
አሴክ ሚሞሳስ (ኮትዲቯር) 0-1 ዋይዳድ ክለብ አትሌቲክ (ሞሮኮ)
ኢነምባ ኢንተርናሽናል (ናይጄሪያ) 0-1 ዛማሌከ (ግብፅ)
ኢኤስ ሴቲፍ (አልጄሪያ) 0-2 ማሜሎዲ ሰንዳውንስ (ደቡብ አፍሪካ) [የሴቲፍ ደጋፊዎች በፈጠሩት ረብሻ ጨዋታው በመቋረጡ ካፍ ሴቲፍን ከቻምፒየንስ ሊጉ ውጪ ያደረገ ሲሆን ውጤቱም ተሰርዟል፡፡]
ማክሰኞ ሰኔ 22/2008
22፡00 – አል አሃሊ (ግብፅ) ከ አሴክ ሚሞሳስ (ኮትዲቯር) (ቦርግ ኤል አረብ ስታዲየም)