ቻምፒዮንስ ሊግ፡ አል አህሊ በሜዳው በአሴክ ሚሞሳስ ሲሸነፍ ባምላክ ተሰማ ዛሬ ያጫውታል

በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ ቦርግ ኤል አረብ ስታዲየም ላይ አሴክ ሚሞሳስን ያስተናገደው አል አሃሊ 2-1 ተረትቶ ወደ ግማሽ ፍፃሜ የሚወስደውን መንገድ ፈተና አድርጎበታል፡፡ ከጨዋታው በፊት ሰፊ የማሸነፍ ግምት አግኝተው የነበሩት ቀያዮቹ ሰይጣኖች በጥቁርን እና ቢጫዎቹ በሜዳቸው ተሸንፈዋል፡፡

15 ሺህ የአሃሊ ደጋፊዎች በተከታተሉት ጨዋታ ያኒክ ዛክሪ በመጀመሪያው አጋማሽ አሴክን ቀዳሚ ሲያደርግ የቀድሞ የፊዮረንቲና እና ፔሩጂያ የመሃል ተከላካይ አህመድ ሄጋዚ አሃሊን የሁለተኛው አጋማሽ እንደጀመረ አቻ ማድረግ ችሏል፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ 10 ደቂቃዎች ሲቀሩት የአሃሊው ግብ ጠባቂ ሻሪፍ ኤክራሚ የሰራውን ስህተት ተጠቅሞ አርማንድ ኒያምኬ የአሴክን የድል ግብ ከቅርብ እርቀት አስቆጥሯል፡፡ ውጤቱን ተከትሎ አሴክ ሚሞሳስ በሶስት ነጥብ ሶስተኛ ሲሆን ሁለት ተከታታይ ሽንፈት የደረሰበት አሃሊ ያለምንም ነጥብ የምድቡ ግርጌ ላይ ይገኛል፡፡

PicsArt_1467188362647

የምድብ ጨዋታዎቹ ዛሬ ሲቀጥሉ ራባት ላይ የምድብ አንድን የበላይነት ለመውሰድ ዋይዳድ ካዛብላንካ ዜስኮ ዩናይትድን ያስተናግዳል፡፡ ኢትዮጵያዊያኑ ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ፣ ረዳቶቹ ክንዴ ሙሴ እና ተመስገን ሳሙኤል ካፍ ጨዋታውን እንዲመሩ መርጧቸዋል፡፡ ዋይዳድ ከሜዳው ውጪ አቢጃን ላይ በምድብ መክፈቻ ጨዋታ አሴክ ሚሞስን ያሸነፈ ሲሆን ዜስኮ በሜዳው እና ደጋፊ ፊት አል አሃሊን መርታት ችሏል፡፡ ሁለቱም ክለቦች በቻምፒየንስ ሊግ እስካሁን የተሳካ ጉዞ ማድረጋቸው ከወዲሁ ጨዋታው እንዲጠበቅ አድርጓል፡፡

በምድን ሁለት ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ኢኒምባን ያስተናግዳል፡፡ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ በምድብ መክፈቻ ጨዋታ ከኢኤስ ሴቲፍ ጋር ያስመዘገበው ውጤት በመሰረዙ ኢኒምባን ለማሸነፍ ወደ ሜዳ ይገባል፡፡ የ2014 የአፍሪካ ቻምፒዮኑ ሴቲፍ በደጋፊዎቹ ረብሻ ምክንያት ከአህጉሪቱ ታላቅ የክለቦች ውድድር ውጪ ሆኗል፡፡ የግብፁ ዛማሌክ በሲቴፍ ቅጣት ምክንያት አራፊ ቡድን ነው፡፡ በዛማሌክ በምድብ መክፈቻ ጨዋታ በሜዳው የተረታው ኢኒምባ ወደ ግማሽ ፍፃሜው የማለፍ ተስፋውን ለማለምለም ወደ ሜዳ ይገባል፡፡ ይህ ምድብ ሶስት ክለቦች ብቻን መያዙ ወደ ግማሽ ፍፃሜው ለማለፍ የሚደረገውን ትንቅንቅ ከባድ ያደርገዋል፡፡

 

የማክሰኞ ውጤት

አል አሃሊ (ግብፅ) 1-2 አሴክ ሚሞሳስ (ኮትዲቯር)

 

ረቡዕ ሰኔ 22/ 2008

19፡00 – ማሜሎዲ ሰንዳውንስ (ደቡብ አፍሪካ) ከ ኢኒምባ ኢንተርናሽናል (ናይጄሪያ) (ሉካስ ማስተርፒስስ ሞሪፕ ስታዲየም)

22፡00 – ዋይዳድ አትሌቲክ ክለብ (ሞሮኮ) ከ ዜስኮ ዩናይትድ (ዛምቢያ) (ኮምፕሌክስ ፕሪንስ ሞላይ አብደላ ስታዲየም)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *