ከ2007 የፕሪምየር ሊግ የውድድር ዘመን ጅምሮ በኤሌክትሪክ ቆይታ አድርጓል፡፡ ዛሬ በሚጠናቀቀው የውድድር ዓመትም ለቀዮቹ 10 ግቦችን በማስቆጠር ክለቡን ከወራጅነት ታድጓል፡፡ ናይጄሪያዊው የፊት መስመር ተጫዋች ፒተር ኦክቹኩ ንዋድኬ፡፡
በሃገሩ ናይጄሪያ ለሃርትላንድ እና በደቡብ አፍሪካ ለኬፕ ታውን እና ጆሞ ኮስሞስ የተጫወተው የ26 አመቱ ፒተር ኑዋድኬ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ስለነበረው ጨዋታ እና ተያያዝዥ ጉዳዮች ከጋዜጠኞች ለቀረበለት ጥያቄ መልስ ሰጥቷል፡፡
ከወራጅት ስለመትረፋቸው
በመጀመሪያ ፈጣሪን ማመስገን እፈልጋለው፡፡ የቡድን አጋሮቼን ማመስገን እፈልጋለው፡፡ ምክንያቱም ከወራጅነት ለመትረፍ ያደረግነው ትግል ቀላል አልነበረም፡፡ በጠንካራ ስራ ውጤት ይዘን ለመውጣት ችለናል፡፡ ጨዋታው ከነበረው ትርጉም አንፃር ፈታኝ ነበር፡፡ ሁሉም ሰው ውጤትን ይጠብቅ ነበር ምክንያቱም ውጤት ካላመጣን እንወርድ ነበር፡፡
ኤሌክትሪክ በተደጋጋሚ ላለመውረድ ስለመጫወቱ
ምን እንደምል አላውቅም፡፡ ይህ እግርኳስ ነው፡፡ ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾችን ይዘናል ፤ ነገር ግን ውጤት ልናመጣ አልቻልንም፡፡ በሚቀጥለው ዓመት በወራጅ ቀጠናው ውስጥ ላለመገኘት እንጫወታለን፡፡
ስለቀጣይ ማረፊያው
ስለቀጣዩ ማረፊያዬ አሁን ላይ ምንም ማለት አልችልም አሁን እኔ ምፈለገው እረፍት ማድረግን ነው፡፡ ስዝውውር ሰዓቱ ሲደርስ እናወራለን፡፡
አንድ ዓመት ከስድስት ወር ስላሳለፈበት የኢትዮጵያ እግርኳስ
በኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካ እግርኳስ መካከል ግልፅ የሆነ ሰፊ ልዩነት አለ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሶስት ወይም ሁለት ሜዳዎች ናቸው ለፕሪምየር ሊጉ ብቁ የሆኑት፡፡ ጥሩ ሜዳዎች በሌሉበት እንዴት አድርገህ ጥሩ ተፎካካሪ ትሆናለህ፡፡ የእግርኳስ ዋነኛ መሰረት ሜዳ ነው፡፡ ጥሩ ሜዳ ካለህ ጥሩ እግርኳስ መጫወት ትችላለህ፡፡