የኢትዮጵያ ፕሪሚር ሊግ የ2008 የውድድር ዘመን ዛሬ ሁለት ጨዋታ እና የመዝጊያ ስነስርአት አስተናግዶ ተጠናቋል፡፡ቅዱስ ጊዮርጊስም የኮከብነት ሽልማቶችን ጠራርጎ ወስዷል፡፡
08፡30 ላይ ደደቢት ሀዲያ ሆሳዕናን አስተናግዶ 4-1 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፏል፡፡ የደደቢትን የድል ግቦች ዳዊት ፍቃዱ ሁለት ፣ ሄኖክ ኢሳያስ እና ሳሚ ሳኑሚ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ሁለት ግቦች ከመረብ ያሳረፈው ዳዊት ፍቃዱ የግብ መጠኑን 14 በማድረስ በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ሰንጠረዡ ከቀድሞ የቡድን አጋሩ ታፈሰ ተስፋዬ በአንድ ግብ ብቻ በማነስ 2ኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል፡፡
10፡30 ላይ ሀዋሳ ከተማን ያስተናገደው ቻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ 2-1 በማሸነፍ በድል ዋንጫውን ተቀብሏል፡፡ ሀዋሳ ከተማ ተጫዋቾች የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾችን በክብር በማጀብ ወደ ሜዳ የገቡ ሲሆን ጫማውን እንደሚሰቅል ይፋ ያደረገው ሙሉጌታ ምህረት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ስጦታ ተበርክቶለታል፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስን ግቦች አዳነ ግርማ እና ራምኬል ሎክ ከመረብ ሲሳረፉ የሃዋሳን ብቸኛ ግብ ሙሉጌታ ምህረት በፍፁም ቅጣት ምት ከመረብ በማሳረፍ የጨዋታ ዘመኑን በጎል ቋጭቷል፡፡
ውጤቱን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ26 ጨዋታ 55 ነጥቦች በመሰብሰብ የውድድር ዘመኑን በቻምፒዮንነት አጠናቋል፡፡
ከጨዋታው በኋላ ለውድድሩ መሳካት አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት የምስክር ወረቀት የተሰጠ ሲሆን ለውድድር ዘመኑ ኮከቦችም ሽልማት ተሰጥቷል፡፡
የውድድር ዘመኑ ኮከቦች ሽልማት የሚከተለውን ይመስላል፡-
ኮከብ አሰልጣኝ
ማርት ኑይ (ቅዱስ ጊዮርጊስ) – 25,000 ብር
ኮከብ ተጫዋች
አስቻለው ታመነ (ቅዱስ ጊዮርጊስ) -25,000 ብር
ኮከብ ግብ አግቢ
ታፈሰ ተስፋዬ (አዳማ ከተማ – በ15 ግቦች) – 25,000 ብር
ኮከብ ግብ ጠባቂ
ሮበርት ኦዶንካራ (ቅዱስ ጊዮርጊስ) – 15,000 ብር
ኮከብ ረዳት ዳኛ
ክንዴ ሙሴ – 8000 ብር
ኮከብ ዳኛ
በላይ ታደሰ – 10,000 ብር
የስፖርታዊ ጨዋነት ተሸላሚ
መከላከያ የስፖርታዊ ጨዋነት ተሸላሚ ሆኗል፡፡
ልዩ ሽልማት
ሙሉጌታ ምህረት – 10,000 ብር