የ2008 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኮከብ ግብ ጠባቂ ሽልማትን ዩጋንዳዊው ኢንተርናሽናል ሮበርት ኦዶንካራ ለአምስተኛ ተከታታይ ጊዜ ማሸነፍ ችሏል፡፡ የቀድሞ የስፖርት ክለብ ቪላ ግብ ጠባቂው ሮበርት ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የተዛወረው በ2003 አጋማሽ ሲሆን ሊጉ የኮከብ ግብ ጠባቂ መሸለም ከተጀመረበት ከ2003 ጀምሮ (የ2003 ኮከብ ግብ ጠባቂ ሲሳይ ባንጫ ነበር) አምስት ግዜ በመውሰድ ባለሪከርድ ነው፡፡
ፈረሰኞቹ በ26 ጨዋታዎች የተቆጠረባቸው ግብ 12 ብቻ ሲሆን ለዚህም የጠንካራ ተከላካይ መስመራቸው እና የግብ ጠባቂያቸው ብቃት ላቅ ያለ ድርሻን ይወስዳል፡፡ የዩጋንዳ ብሄራዊ ቡድን ሁለተኛ ግብ ጠባቂ የሆነው ሮበርት ስለሽልማቱ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርጓል፡፡
ለአምስተኛ ግዜ በመሸለሙ የተሰማው ስሜት
እኔ እንደማስበው ከሆነ ሁሌም አሸናፊ ስትሆን ደስታ ይሰማሃል፡፡ ብዙዎች ሻምፒዮን ለመሆን ሞክረው አልተሳካላቸውም እና ሻምፒዮን መሆን መታደል ነው፡፡ ፌድሬሽኑ ለሰጠኝ ዕውቅና ማመስገን እፈልጋለው፡፡ ለአምስተኛ ጊዜ ኮከብ መባሌ ምንያህል ጠንክሬ እንደምሰራ ያሳያል፡፡ እንደዘናጋ አያደርገኝም ፤ ግን ጠንክሬ ሰርቼ ተጨማሪ ሽልማቶችን እንዳሸንፍ ይረዳኛል፡፡ ከሁሉም በላይ ያለጊዮረጊስ ደጋፊዎች ድጋፍ ይህንን ሽልማት አላገኝም ነበር፡፡ ክለቡ በኔ ላይ ዕምነት ስላለው እና ደጋፊዎቹ ለሰጡኝ ድጋፍ ለመሰግናቸው እወዳለው፡፡
ከዩጋንዳው ግብ ጠባቂ ዴኒስ ኦኒያንጎ ተከትሎ የፕሪምየር ሊግ አሸናፊ መሆኑ
የነገሮች መገጣጠም አይደለም፡፡ ዩጋንዳ ጥሩ ብቃት ያላቸውን ግብ ጠባቂዎች የምታፈራ ሃገር ነች፡፡ ስለዚህ የእኔ የፕሪምየር ሊጉ ሻምፒዮን መሆን የሚደንቅ አይደለም፡፡
በዩጋንዳ እያለው ጠንክሬ እሰራ ነበር፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያንን ተመልክቶ ነው ወደ ኢትዮጵያ ያመጣኝ፡፡ ዴኒስም የደቡብ አፍሪካ ሊግ ኮከብ ግብ ጠባቂ ሆኖ ተመርጧል፡፡ ይህ ለዩጋንዳ የተለየ ስፍራ እንዲሰጥ ያደርጋል፡፡ ካስታወስከ የሴካፋ ዋንጫ ኮከብ ግብ ጠባቂም (ኢስማኤል ዋቴንጋ) ከዩጋንዳ ነበር፡፡
ሃገሩ ጥሩ ብቃት ያላቸውን ግብ ጠባቂዎች ስለማፍራቷ
እውነት ለመናገር ዕምቅ ችሎታው አለ፡፡ ነገር ግን ያለጥሩ አሰልጣኝ ጥሩ ግብ ጠባቂ ማግኘት አልቻልም፡፡ እኛ ጋር በጣም ጥሩ የግብ ጠባቂ አሰልጣኞች አሉን፡፡ ሁሌም እራሳችንን እንድናሻሽል ይገፉናል ይረዱናል፡፡ ችሎታው ካለህ ደግሞ ከጥሩ ስልጠና ጋር ትልቅ ደረጃ መድረስ ይቻላል፡፡ አብዛኞቹ ግብ ጠባቂዎቻችን ህልማቸውን ለማሳከት ትጉህ ስለሆኑ ሁሌም ዩጋንዳ ጥሩ ብቃት ያላቸው ግብ ጠባቂዎች ማፍራት እየቻለች ነው፡፡ ያለማጋነን ከሌሎቹ ሃገራት በተሻለ ግብ ጠባቂዎች ላይ ጠንካራ ስራ እየሰራን ነው፡፡
ስለኢትዮጵያ ቆይታው
ከሃገር ውጪ ስትጫወት ሁሌም የተለየ ነው፡፡ ዓየሩን፣ ደጋፊዉን፣ የህዝቡን የአኗኗር ሁኔታ እና ምግቡን መላመድ አለብህ፡፡ ከብዙ ጉዳዮች አንፃር ኢትዮጵያ እና ዩጋንዳ ይለያያሉ፡፡ ነገር ግን እግርኳስ ተጫዋች ከሆንክ እነዚህን ፈተናዎች ማለፍ የግድ ይለሃል፡፡ እኔ ለምሳሌ በአንድ ሊግ ውስጥ ከገባሁ በኃላ ለመልመድ አልችገርም፡፡ ዋነኛው ቁም ነገር ጥሩ ተንቀሳቅሰህ ውጤትን ማምጣት ነው፡፡