የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ትላንት ፍፃሜውን ሲያገኝ ታፈሰ ተስፋዬ በ15 ግቦች የውድድር ዘመኑን በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት አጠናቋል፡፡
ሀዋሳ ከተማን ለቆ ዘንድሮ አዳማን የተቀላቀለው ታፈሰ ለ5ኛ ጊዜ በኮከብ ግብ አስቆጣሪነት በማጠናቀቅ ታሪክ ሰርቷል፡፡
ታፈሰ ትላንት የኮከብ ግብ አግቢነት ሽልማቱን ከወሰደ በኋላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
በድጋሚ ወደ ኮከብ ግብ አግቢነት ክብር በመመለስህ ምን ተሰማህ?
” ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ሆኜ በማጠናቀቄ ከፍተኛ ደስታ ነው የተሰማኝ፡፡ ከስድስት አመት ቆይታ በድጋሚ ወደ ኮከብነት መመለሴ ለኔ ክብር ነው፡፡ በዚህም በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ ”
በኢትዮዽያ ፕሪሚየር ሊግ ታሪክ አምስት ጊዜ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ በመሆን ብቸኛ ተጫዋች በመሆንህ ምን ይሰማሃል?
“ራሴን እንዲህ ነኝ ብዬ በማሰብ እንድዘናጋ አልፈልግም፡፡ አሁን የማስበው ለ2009 ጥሩ ነገር ለመስራት ነው፡፡ አሁን ይሄን አገኘው ብዬ ቁጭ አልልም ፤ ሁሌም ጥሩ ከሰራው ጥሩ ነገር አመጣለው ብዬ ነው የማስበው፡፡ ነገር ግን እንደማንኛውም ሰው ውስጤ ደስ ይለዋል፡፡ ለነገም ስራዬ ያነሳሳኛል ብዬ አስባለው፡፡”
ለአመታት በወጥነት ጎል ታስቆጥራለህ፡፡ ይህን አቋምህን ጠብቀህ የመቆየትህ ሚስጢር ምድነው ?
“ዋናው ትልቁ ነገር ራስህን መጠበቅ እና ለስራው ትልቅ ቦታ ሰጥተህ መስራት እንዲሁም ስራውን ማክበር ያስፈልጋል፡፡ እኔ ጋር ስራ ላይ ቀልድ የለም ፤ ስራዬን አከብራለው፡፡ ስራህን ካከበርክ ስራው ራሱ ያከብርሃል፡፡ ይህን ያህል አመት የመጫወቴ እና በወጥነት ጎል የማስቆጠሬ ሚስጢር ይሄ ነው፡፡ ”
በ2003 ወደ የመን አምርተህ ከተመለስክ በኃላ ብዙም ስኬታማ አመታት አላሳለፍክም፡፡
” ከየመን ከተመለስኩ በኃላ በኢትዮጵያ ቡና ከአሰልጣኙ ጋር በነበረኝ አለመግባባት ጥሩ ጊዜ ማሳለፍ አልቻልኩልም እንጂ የአቋም መውረድ አጋጥሞኝ አልነበረም፡፡ በወቅቱ የነበረው አሰልጣኝ ይከተለው የነበረው ታክቲክ ለኔ ስላልተመቸኝ እንጂ በተሰለፍኩበት ጨዋታ ጎል አስቆጥር ነበር፡፡
” ከስድስት አመት በኃላ ወደ ኮከብነት የተመለስኩት አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በኔ እምነት ስላለውና ወደ ጥሩ አቋም እንድመለስ ስለለፋብኝ ነው፡፡ የአሰልጣኝ አሸናፊ ጥረት ወደ ኮከብነት እንድመለስ ረድቶኛል፡፡ ”
ለአመታት በፕሪሚየር ሊጉ በርካታ ግብ የሚያስቆጥሩ ተጫዋቾች በቁጥር ጥቂት ናቸው፡፡ የሚቆጠረው የጎል መጠንም እያነሰ መጥቷል…
” የጎሉ ቁጥር ማነስ የሀገራችን ቡድኖች የሚከተሉት አጨዋወት በአንድ አጥቂ ላይ መሰረት ያደረገ በመሆኑ ነው፡፡ የጎሉም መጠን ከዚህ በኃላ እያነሰ ነው የሚሄደው፡፡
ሌላው አጥቂ ላይ መሰራት አለበት፡፡ እኛም ያዳበርነው በተፈጥሮ ካገኘነው ተነስተንና በተወሰነ መልኩ አሰልጣኝ የደገፈን ነው፡፡ በአሁን ሰአት በሃገራችን በግብ ጠባቂ እና አጥቂ ስፍራ ከፍተኛ ክፍተት አለ፡፡ ባለፈው አመት ኮከብ ጎል አስቆጣሪ እና ግብ ጠባቂ ሆነው የጨረሱት የውጪ ዜጎች ነበሩ፡፡ ተመራጭ እየሆኑ ያሉትም ከውጭ የሚመጡት መሆናቸው ያለውን ክፍተት ያሳያል፡፡ ስለዚህ በግብ ጠባቂ እና አጥቂዎች ላይ ከፍተኛ ስራ መስራት ይኖርብናል፡፡ ”
ከታፈሰ በሚቀጥለው አመት ምን እንጠብቅ?
” ከፈጣሪ ጋር አቅሜ እስከፈቀደ ድረስ አቋሜን ጠብቄ አሁንም እታገላለው፡፡ ለሀገሬም ፣ ለሚመጣውም ትውልድ መልካም ነገር አስቀምጬ ማለፍ እፈልጋለው፡፡ ወጣቱን ፣ የቡድን አጋሮቼን ፣ በሌላ ክለብ የሚጫወቱትን እና በመንገድ ላይ የሚያናግሩኝን ሁሉ በራሳቸው መንገድ በመሄድ እንዲሁም ራሳቸውን መጠበቅ ያሰቡበት መድረስ እንደሚችሉ ማሳየት እፈልጋለሁ፡፡ ”
ትላንት ሙሉጌታ ምህረት በክብር መሸኘቱ ምን አይነት ስሜት ፈጠረብህ?
” ወደፊት እኛም መጫወት ስናቆም በእንደዚህ ሁኔታ ቢሆን በጣም ደስ ይላል፡፡ ይህን ስሰማ በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡ አንድ እግርኳስ ተጨዋች በማቆሚያው ሰአት በክብር ሊሸኝ ይገባል፡፡ ይህም ተግባር ሊለመድ ይገባል፡፡
” እኔ ዛሬ (ረቡዕ) ሽልማት ለመቀበል ወደ ሜዳ ስገባ የጊዮርጊስ ደጋፊ አክብሮ ሲቀበለኝ በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡ ወደፊትም መለመድ አለበት፡፡
” ወደ አንድነት መምጣትና ፉትቦሉን ለማሳደግ እጅ ለእጅ ተያይዘን መሄድ አለብን፡፡ ”