የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ2008 የውድድር ዘመን ትላንት ፍጻሜውን ሲያገኝ ታፈሰ ተስፋዬ በ15 ግቦች የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ክብርን ተጎናፅፏል፡፡ የፕሪሚየር ሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች ዝርዝር እና ተያያዥ እውነታዎችን እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል፡፡
የመጀመርያው ሽልማት
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በውድድር ዘመኑ በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት የሚያጠናቅቁ ተጫዋቾችን በመሸለም እውቅና መስጠት የጀመረው በ1977 ነበር፡፡ የመጀመርያው ተሸላሚም የቅዱስ ጊዮርጊሱ ሙሉጌታ ከበደ ነበር፡፡
ከአንድ ጊዜ በላይ የኮከብ ግብ አስቆጣሪነት ክብር ያገኙ ተጫዋቾች
ታፈሰ ተስፋዬ ለ5 ጊዜያት ያህል ከፍተና ግብ አስቆጣሪ ሆኖ በማጠናቀቅ ተወዳዳሪ አልተገኘለትም፡፡ ታፈሰ በኤሌክትሪክ (1) ፣ ኢትዮጵያ ቡና (2) እና በአዳማ ከተማ (1) ማልያዎች ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ አጠናቋል፡፡ ዮርዳኖስ አባይ ፣ ሙሉጌታ ከበደ እና አህመድ ጁንዲ 3 ጊዜ ሲያገኙ ጌቱ ከበደ ፣ አሰግድ ተስፋዬ ፣ አዳነ ግርማ እና ጌታነህ ከበደ 2 ጊዜ አግኝተዋል፡፡
በአንድ የውድድር ዘመን በርካታ ግብ
ዮርዳኖስ አባይ በ1993 የውድድር ዘመን 24 ግቦች አስቆጥሮ እስካሁን ያልተሰበረ ሪኮርድ ይዟል፡፡ ታፈሰ ተስፋዬ በ2001 የውድድር ዘመን ፣ አዳነ ግርማ በ2004 የውድድር ዘመን 23 ግቦች በማስቆጠር ይከተላሉ፡፡
በተከታታይ ያሸነፉ ተጫዋቾች
ዮርዳኖስ አባይ ለ3 ተከታታይ አመታት በኮከብ ግብ አግቢነት በማጠናቀቅ ቀዳሚው ተጫዋች ነው፡፡ ዮርዳኖስ በ1993 ፣ 94 እና 95 በከፍተኛ ግብ አግቢነት አጠናቋል፡፡ ሙሉጌታ ከበደ ፣ ጌቱ ከበደ ፣ አሰግድ ተስፋዬ እና ታፈሰ ተስፋዬ ለ2 ተከታታይ አመታት ተሸልመዋል፡፡
አህመድ ጁንዲ
የቀድሞው የምድር ባቡር ኮከብ 3 ጊዜ በኮከብ ግብ አስቆጣሪነት ቢያጠናቅቅም ሁሉንም ሽልማቶች በአስገራሚ ሁኔታ ከሌሎች ጋር ተጋርቷል፡፡ አህመድ በ1988 ከአሰግድ ተስፋዬ ጋር ፣ በ1995 ከዮርዳኖስ አባይ ጋር ፣ በ1996 ከታፈሰ ተስፋዬ እና መሳይ ተፈሪ ጋር ኮከብነት ሽልማቱን ተጋርቷል፡፡
ብቸኛው የውጭ ዜጋ
በ2007 የውድድር ዘመንን በኮከብ ግብ አግቢነት ያጠናቀቀው ናይጄርያዊው ሳሙኤል ሳኑሚ ይህንን ክብር የወሰደ ብቸኛው የውጭ ዜጋ ነው፡፡ የደደቢቱ ሳኑሚ በ22 ግቦች የውድድር ዘመኑን በኮብ ግብ አግቢነት ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡
በርካታ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ የያዙ ክለቦች
የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች 10 ጊዜያት ያህል በኮከብ ግብ አስቆጣሪነት ሲያጠናቅቁ ፣ የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች 7 ፣ የኤሌክትሪክ እና ምድር ጦር ተጫዋቾች 4 ጊዜ አሸንፈዋል፡፡
ለትውስታ
ፕሪሚየር ሊጉ በአዲስ መልክ ከተዋቀረበት 1990 ጀምሮ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን ያጠናቀቁት የሚከተሉት ናቸው
1990. ሀሰን በሽር (ኢትዮጵያ መድን) – 8
1991. በረከት ሀጎስ (ሀዋሳ ከተማ) – 8
1992. ስንታየሁ ጌታቸው (ቅዱስ ጊዮርጊስ) – 8
1993. ዮርዳኖስ አባይ (ኤሌክትሪክ) – 24
1994. ዮርዳኖስ አባይ (ኤሌክትሪክ) – 20
1995. ዮርዳኖስ አባይ (ኤሌክትሪክ/ኢትዮጵያ ቡና) – 14
አህመድ ጁንዲ (ምድር ባቡር) – 14
1996. መሳይ ተፈሪ (አርባምንጭ ጨጨ) – 13
ታፈሰ ተስፋዬ (ኤሌክትሪክ) – 13
አህመድ ጁንዲ (ምድር ባቡር) – 13
1997. መዳህኔ ታደሰ (ትራንስ ኢትዮጵያ) – 18
1998. ታፈሰ ተስፋዬ (ኢትዮጵያ ቡና) – 21
1999. (በውድድር ዘመኑ አጋማሽ 10 ክለቦች አቋርጠው እስኪወጡ ድረስ ታፈሰ በ11 ግብ ይመራ ነበር፡፡ በወቅቱ ለኮብ ግብ አግቢ ሽልማት አልተሰጠም)
2000. ሳላዲን ሰኢድ (ቅዱስ ጊዮርጊስ) – 21
2001. ታፈሰ ተስፋዬ (ኢትዮጵያ ቡና) – 23
2002. ታፈሰ ተስፋዬ (ኢትዮጵያ ቡና) – 21
2003. አዳነ ግርማ (ቅዱስ ጊዮርጊስ) – 20
ጌታነህ ከበደ (ደደቢት) – 20
2004. አዳነ ግርማ (ቅዱስ ጊዮርጊስ) – 23
2005. ጌታነህ ከበደ (ደደቢት) – 22
2006. ኡመድ ኡኩሪ (ቅዱስ ጊዮርጊስ) – 16
2007. ሳሙኤል ሳኑሚ (ደደቢት) – 22
2008. ታፈሰ ተስፋዬ (አዳማ ከተማ) – 15