ድሬዳዋ ከተማ አሰልጣኝ መሰረት ማኒ እና ረዳታቸው ኃይማኖት ግርማን ከሃላፊነት ማንሳቱን ሶከር ኢትዮጵያ ለክለቡ ቅርበት ካላቸው ምንጮች ያገኘችው መረጃ ያመለክታል፡፡
በ2007 ድሬዳዋ ከተማን ከ4 አመት የብሄራዊ ሊግ ቆይታ በኋላ ወደ ፕሪሚየር ሊግ እንዲያድግ ያደረገችው አሰልጣኝ መሰረት ማኒ በዘንድሮው የውድድር ዘመን የመጀመርያ ዙር ክለቡን በጥሩ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ ማድረግ ችላ ነበር፡፡ በሁለተኛው ዙር ድሬዳዋ ከፍተኛ የሆነ የውጤት ቀውስ ውስጥ በመግባት በሊጉ 11ኛ ሆኖ ለማጠናቀቅ መገደዱ ለአሰልጣኝ መሰረት ስንብት ምክንያት መሆኑ ተገልጿል፡፡
ሰሞኑን በተደጋጋሚ ስብሰባዎችን በማድረግ ተጠምዶ የሰነበተው የክለቡ የቦርድ አመራር የሚመለከታቸውን አካላት በመጥራት የድክመታቸውን ምንጭ ከገመገመ በኋላ ከፍተኛ ልምድ እና የውጤታማነት ሪከርድ ያለው አሰልጣኝ ለማምጣት በመወሰኑ አሰልጣኝ መሰረት ማኒ አና ረዳት አሰልጣኙ ኃይማኖትን ማሰናበቱን ነገ በይፋ በደብዳቤ የሚያሳውቅ መሆኑን ለክለቡ ቅርበት ያላቸው አካላት ለሶከር ኢትዮዽያ ተናግረዋል፡፡
አሰልጣኝ መሰረት ማኒ የኢትዮዽያውያን የስፖርት ፌሲቲቫል ላይ ለመካፈል በቀረኘበላት ግብዧ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ያቀናች ሲሆን ከ22 ቀናት በኋላ እንደምትመለስ ቢታወቅም በድጋሚ በቀረበላት የስልጠና ግብዣ ተመልሳ ለ3 ወር ወደ አሜሪካ የምታቀና ይሆናል፡፡
አሰልጣኝ መሰረት በአሜሪካ ቆይታ ማድረጓ እንድትሰናበት መድረጉ አልያም መሰናበቷን በማወቋ ምክንያት ወደ አሜሪካ የተጓዘች መሆኗ የተረጋገጠ ነገር የለም፡፡ ነገር ግን ወደ አሜሪካ ስትጓዝ ተጨዋቾቿን እንደተሰናበተች ለአሰልጣኟ ቅርበት ያላቸው ሰዎች ገልፀውልናል፡፡
የአሰልጣኟ ከድሬደዋ ከተማ ጋር የመለያየቷ ነገር እርግጥ የሚሆን ከሆነ ፕሪሚየር ሊጉ የሃገሪቱ ትልቅ ሊግ ላይ የሚገኝ ቡድን በመምራት በታሪክ መዝገብ ላይ በብቸኝነት የሰፈረችው አሰልጣኝ መሰረት ማኒን የሚያጣ ይሆናል፡፡