ቅዱስ ጊዮርጊስ እና መከላከያ ለሊግ ዋንጫ ፍፃሜ ደረሱ

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ጥሎ ማለፍ (ሊግ ዋንጫ) ግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ዛሬ ተካሂደው ቅዱስ ጊዮርጊስ እና መከላከያ ወደ ፍጻሜው ተሸጋግረዋል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቻምፒዮን በመሆኑ ጦሩ ከወዲሁ ለ2017 የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ማለፉን አረጋጧል፡፡

07:00 ላይ አዳማ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያደረጉት ጨዋታ መደበኛ ክፍለ ጊዜ 1-1 ተጠናቆ ቅዱስ ጊዮርጊስ በመለያ ምቶች አሸንፏል፡፡

በቅድሚያ መርሃ ግብሩ ሲወጣ 08:00 እንደሚካሄድ በመነገሩ የመጀመርያው አጋማሽ አመዛኝ ደቂቃዎች ቁጥሩ አነስተኛ የሆነ ተመልካች የተከታተለው ሲሆን ሰአቱ ወደ 08:00 ሲቃረብ ተመልካቹ በብዛት መግባት ጀምሯል፡፡

PicsArt_1467732947161

ግብ በማስቆጠሩ ቅድሚያውን የወሰዱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ሲሆኑ በ40ኛው ደቂቃ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ሳላዲን ሰኢድ ወደ ግብነት ለውጦታል፡፡ የመጀመርያው አጋማሽም በቅዱስ ጊዮርጊስ መሪነት ተጠናቋል፡፡

ከእረፍት መልስ ከሙሉ ብልጫ ጋር ጫና ፈጥረው የተጫወቱት አዳማ ከተማዎች በ61ኛው ደቂቃ በሱሌማን መሃመድ አማካኝነት አቻ መሆን ችለዋል፡፡ አዳማዎች ከግቡ በኋላ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ቢያደርጉም ተጨማሪ ግብ ሳያገኙ ጨዋታው በአቻ ውጤት ተፈጽሟል፡፡

PicsArt_1467732853223

አሸናፊውን ለመለየት በቀጥታ ወደ መለያ ምቶች ሲያመሩ ሁለቱም ቡድኖች የመጀመርያዎቹን 4 መለያ ምቶች ወደ ግብነት ቀይረዋል፡፡ ሞገስ ታደሰ የመጨረሻውን መለያ ምት ሲስት አዳነ ግርማ አስቆጥሮ በቅዱስ ጊዮርጊስ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ፈረሰኞቹም ሀሙስ ለሚደረገው ፍጻሜ አልፈዋል፡፡

ከጨዋታው አስቀድሞ በፀጥታ ረገድ ስጋት ቢኖርም የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ አባላት በቦታው በመገኛት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር ጨዋታው በሰላም እንዲጠናቀቅ ተደርጓል፡፡

PicsArt_1467732597254

09:45 ላይ የተጀመረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና መከላከያ ጨዋታ በመከላከያ የበላይነት ተጠናቋል፡፡

በሊግ ዋንጫው የቅርብ አመታት ጥንካሬውን እያሳየ የመጣው መከላከያ በአዲሱ ተስፋዬ የ7 ደቂቃ ግብ ቀዳሚ መሆን ሲችል ፍሬው ሰለሞን በ39ኛ ደቂቃ ሁለተኛውን አክሎ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

ከእረፍት መልስ ንግድ ባንኮች ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ጎል ለማግኘት ጫና ቢፈጥሩም የተሻለ የግብ እድል መፍጠር የቻሉት መከላከያዎች በሳሙኤል ታዬ አማካኝነት አስቆጥረው ጨዋታውን በ3-0 አሸናፊነት ደምድመዋል፡፡ ጦሩ በሊጉ ዋንጫ በ4 አመት ውስጥ ለ3ኛ ጊዜ የፍጻሜ ተፋላሚ መሆኑንም አረጋግጧል፡፡ መከላከያም በመጪው አመት የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳታፊ መሆኑን ማረጋገጥ ችሏል፡፡

PicsArt_1467732998580

የፍጻሜ ጨዋታው በመጪው ሀሙስ በቅዱስ ጊዮርጊስ እና መከላከያ መካከል አዳማ አበበ ቢቂላ ላይ ይካሄዳል፡፡

PicsArt_1467732894090

በስፍራው የነበሩት የቅዱስ ጊዮርጊስ ማኔጅመት አባላት የአዳማ ደጋፊዎች ማህበር የመጡትን የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎቸን በክብር ተቀብለው በሰላም እንዲመለሱ በማድረጋቸው አመስግነዋል፡፡

PicsArt_1467732698863

የመከላከያ የልብ ደጋፊዎች አዳማ በመምጣት ቡድናቸውን አበረታተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *