የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን መቀመጫውን ፓርማ ካደረገው የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያ ኢርያ ጋር የትጥቅ አቅርቦት ውል ተፈራርሟል፡፡
የፌዴሬሽኑ የፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንድምኩን አላዩ እንዲሁም የፌዴሬሽኑ የፋይናንስ ኃላፊ አቶ ነብዩ እና ኮሎኔል አምሳሉ ወደ ጣልያን በማቅናት ከኩባንያው ጋር ለአንድ ሳምንት ባደረጉት ድርድር ከስምምነት ላይ የደረሱ ሲሆን ለቀጣዮቹ 2 አመታትም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የኢሪያ ትጥቆችን ለብሶ ወደ ሜዳ የሚገባ ይሆናል፡፡
ፌዴሬሽኑ ለትጥቅ አቅርቦቱ በአመት 90 ሺህ ዩሮ ክፍያ የሚፈጽም ሲሆን ኩባንያው ደግሞ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በሁሉም የእድሜ እርከኖች እና ሁለቱም ጾታዎች የሚጠቀምባቸውን ትጥቆች በሶስት አይነት ቀለማት ለማቅረብ ተስማምቷል፡፡
ኩባንያው ያዘጋጀው የብሄራዊ ቡድኑ ትጥቅ ይህንን ይመስላል፡-
1ኛ መለያ – አረንጓዴ ማልያ ፣ ቢጫ ቁምጣ እና ቀይ ካልሲ
2ኛ መልያ – ቢጫ ማልያ ፣ አረንጓዴ ቁምጣ እና ቀይ ካልሲ
3ኛ መልያ – ቀይ ማልያ ፣ ቢጫ ቁምጣ እና አረንጓዴ ካልሲ
በ1988 የተመሰረተው ኢርያ የስፖርት ቁሳቁስ አምራች ኩባንያ መቀመጫውን ፓርማ ያደረገ ሲሆን ከዚህ ቀደም ለቅዱስ ጊዮርጊስ ትጥቆች ሲያቀርብ መቆየቱም ይታወሳል፡፡
በአሁኑ ወቅትም ለፕሪሚየር ሊጉ ክለብ ኖርዊች ሲቲ ፣ በአውሮፓ ዋንጫ የብዙዎቹን ቀልብ የገዛው አይስላንድ ብሄራዊ ቡድን ፣ ፔስካራ ፣ ፓርማ ፣ ሚልዎል እና የሩዋንዳ ብሄራዊ ቡድን የኢርያ ትጥቆችን ከሚጠቀሙ ቡድኖች መካከል ይገኙበታል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለረጅም አመታት የአዲዳስ ምርቶችን ሲጠቀም የኖረ ሲሆን በቅርቡ የአውስትራሊያው ኤኤምኤስ ክሎዚንግ የብሄራዊ ቡድኑ ትጥቅ አቅራቢ ለመሆን በድርድር ላይ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡