ወላይታ ድቻ ከዚህ ቀደም እንደተለመደው ሁሉ በዘንድሮው ክረምትም በተጫዋች ግዢ ላይ ከፍተኛ ገንዘብ እንደማያፈስ ታውቋል፡፡
ስማቸው ከአርባምንጭ ከተማ አሰልጣኝነት ጋር የተያያዙት አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪን በክለቡ ማቆየቱን ያረጋገጠው ወላይታ ድቻ ኮንትራታቸውን ያጠናቀቁ ተጫዋቾችን ውል በማደስ ላይ ትኩረቱን አድርጓል፡፡
ክለቡ በዚህ ሳምንት በውሰት የሚሰጡ እና የሚሰናበቱ እንዲሁም ከተስፋ ቡድን የሚያድጉ ተጫዋቾች ዙርያ ከውሳኔ እንደሚደርስ ይጠበቃል፡፡
የዝውውር ገበያው ዋጋ ጣራ መንካት በወላይታ ድቻ የግዢ ፖሊሲ ላይ ለውጥ እንዳይኖር የሚያደርግ ሲሆን በፕሪሚየር ሊጉ ተጫዋቾች ላይ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ የከፍተኛ ሊግ እና ብሄራዊ ሊግ ተጫዋቾች ላይ ትኩረታቸውን አድርገዋል፡፡ የፕሪሚየር ሊግ ልምድ የሌላቸው ተጫዋቾችን በመሰብሰብ ጠንካራ ቡድን በመፍጠር የሚታወቁት አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ላይም እምነት አሳድሯል፡፡
አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በክልል ከተሞች ተዘዋውረው የከፍተኛ ሊግ ጨዋታዎችን በመመልከት ተጫዋቾችን እየመለመሉ ሲሆን በሀምሌ ወር አጋማሽ የሚጀመረው የብሄራዊ ሊግ ማጠቃለያ ውድድር ላይ ትኩረት አድርገው ለመስራት እንደተዘጋጁ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡