የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ፕሪሚየር ሊግ የማጠቃለያ ውድድር የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ጁነይዲ ባሻ በተገኙበት ተከፍቷል፡፡ በመክፈቻው በተደረጉት ጨዋታዎችም አዳማ ድል ሲቀናው ደደቢት ከ ንግደ ባንክ ነጥብ ተጋርተዋል፡፡
08:00 ላይ ባለሜዳው አዳማ ከተማ መከላከያን 1-0 በማሸነፍ ውድድሩን በድል ከፍቷል፡፡ እምብዛም ማራኪ እንቅስቃሴ ባልታየበት ጨዋታ በእለቱ ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው ኢሳ ንጉሴ የጨዋታው መጠናቀቅያ ፊሽካ ሲጠበቅ ወሳኟን ብቸኛ ጎል አስቆጥሮ አዳማን ለድል አብቅቷል፡፡
በዕለቱ ጨዋታውን የሚመሩት ዋና ዳኛ በጉዳት ምክንያት ጨዋታውን መቀጠል ባለመቻላቸው አራተኛው ዳኛ ቀሪውን ጨዋታ በመምራት አጠናቀዋል፡፡
10:00 ላይ ሲጠበቅ የነበረው የደደቢት እና ንግድ ባንክ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተፈፅሟል፡፡ በወጣቶች እግርኳስ በተገናኙ ቁጥር ከፍተኛ ፉክክር የሚስተናገድበት ይህ ጨዋታ ዛሬም ፍትጊያ እና ሀይል የተቀላቀለበት ጨዋታ አስተናግዷል፡፡
ዳንኤል ጌድዮን ደደቢትን ቀዳሚ ሲያደርግ ገመቺሳ አማኑኤል ንግድ ባንክን አቻ አድርጓል፡፡
በርካታ ቁጥር ያለው የስፖርት ቤተሰብ በተከታተለው ጨዋታ ላይ የስቴዲዮሙ ድባብ ትኩረት ይስብ የነበረ ሲሆን አንድ የውጭ ዜጋ በድጋፍ አሰጣጡ በስቴዲዮሙ የነበሩት ተመልካችን ሲያዝናና ውሏል፡፡
የማጠቃለያ ውድድሩ ነገ ሲቀጥል በምድብ ሀ 08:00 ላይ ሀዋሳ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፤ 10:00 ላይ ሐረር ሲቲ ከ አአ ከተማ ይጫወታሉ፡፡