የኦሬንጅ ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የምድብ አንድ ሶስተኛ መርሃግብር ጨዋታዎች ትላንት ተደርገው ዜስኮ ዩናይትድ አሴክ ሚሞሳስን 3-1 ሲረታ አል አሃሊ ከዋይዳድ ካዛብላንካ ጋር ያለግብ አቻ ተለያይቷል፡፡
በሰሜን ዛምቢያ የምትገኘው ንዶላ ላይ ዜስኮ ዩናይትድን የሚያቆመው ጠፍቷል፡፡ በካፍ ውድድሮች አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው በዛምቢያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮፕሬሽን ስር የሚተዳደረው ዜስኮ ወደ ግማሽ ፍፃሜው ለመጓዝ ጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡ አሴክ ሚሞሳስም እንደተጠበቀው በዜስኮ ሽንፈትን ቀምሷል፡፡
ጃክሰን ሙዋንዛ የአሴክ ተከላካዮችን መዘናጋት በመጠቀም ዜስኮን ቀዳሚ ሲያደርግ ጆን ቺንግአንዱ መሪነቱን ወደ ሁለት ያሰፋበትን ግብ በቅጣት ምት አስቆጥሯል፡፡ ኤስክ ሚሞሳስ ከዕረፍት መልስ ከማዕዘን የተሻገረውን ኳስ ከቀጠናቸው ማራቅ የልቻሉትን የዜስኮ ተከላካዮችን መረበሽ ተከትሎ በየሱፍ ዳኦ ግብ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ቢያደርጉም ኢድሪስ ምቦምቦ የግል ብቃቱን ተጠቅሞ የዜስኮን ሶስተኛ ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡
አሌክሳንድሪያ ላይ የስምንት ግዜ የአፍሪካ ሻምፒዮኑ አል አሃሊ ከዋይዳድ ካዛብላንካ ጋር 0-0 ተለያይቷል፡፡ ወደ ግማሽ ፍፃሜው ለማለፍ የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ ገብቶ የነበረው የግብፁ ሃያል የዋይዳድን ተከላካይ መስመር መስበር ሳይችል ቀርቷል፡፡
አሃሊ በዋሊድ ሱሌማን፣ ሳላ ጎማ እና ኢመድ ሞቲብ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ማድረግ ቢችልም ከምድቡ ለማለፍ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል፡፡ የአቻ ውጤቱን ተከትሎ ዋይዳድ በሰባት ነጥብ የምድቡን መሪነት ሲያጠናክር ዜስኮ ዩናይትድ በስድስት ይከተላል፡፡ አሴክ እና አሃሊ የምድቡን ግርጌ ይዘዋል፡፡ የምድብ ጨዋታው ዛሬ በሚደረግ አንድ ጨዋታ ቀጥሎ ሲውል ዛማሌክ ማሜሎዲ ሰንዳውንስን ያስተናግዳል፡፡ የምድብ ሁለት አናት ላይ የሚገኙት ሁለቱ ክለቦች ወደ ግማሽ ፍፃሜ የማለፍ ተስፋቸው የሰፋ ሲሆን ዛማሌክ ከ2002 በኃላ ለመጀመሪያ ግዜ የቻምፒየንስ ሊጉን ዋንጫ ለማንሳንት ጥሩ ግዜ ላይ ይገኛል፡፡ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ እና ዛማሌክ ዕኩል ሶስት ነጥብ አላቸው፡፡
የቅዳሜ ውጤቶች
ዜስኮ ዩናይትድ (ዛምቢያ) 3-1 አሴክ ሚሞሳስ (ኮትዲቯር)
አል አሃሊ (ግብፅ) 0-0 ዋይዳድ አትሌቲክ ክለብ (ሞሮኮ)
ዕሁድ ሃምሌ 10/2008
19፡30 – ዛማሌክ (ግብፅ) ከ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ (ደቡብ አፍሪካ) (ፔትሮስፖርት ስታዲየም)