የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር ከአንድ ቀን እረፍት በኋላ በ2ኛ የመድብ ጨዋታዎች ተመልሷል፡፡ ረፋድ 2 ጨዋታ ያስተናገደው ውድድር 10:00 ላይም ቀጥሎ ቡታጅራ ከተማ እና ወልቂጤ ከተማ ድል ቀንቷቸዋል፡፡
ባቱ ሜዳ ላይ በተካሄደው የምድብ ለ ጨዋታ ቡታጅራ ከተማ ዲላ ከተማን 1-0 በማሸነፍ የመጀመርያ ድሉን አሳክቷል፡፡ የቡታጅራ ከተማን ብቸኛ የድል ጎል በመጀመርያው አጋማሽ ሳሙኤል ገብሬ አስቆጥሯል፡፡
ውጤቱ ቡታጅራን ለመደገፍ የመጡት በርካታ ደጋፊዎችን አስደስቷል፡፡
በተመሳሳይ 10:00 ላይ ከምድብ ሀ በሼር ሜዳ በተካሄደውና ማራኪ እንቅስቃሴ ከጥሩ የኳስ ፍሰት ጋር በታየበት ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ ሞጆ ከተማን 4-1 በሆነ ሰፊ ጎል አሸንፏል፡፡
የወልቂጤን የድል ጎል ጌታነህ ሙሉነህ (2) ፣ ሚካኤል ጋሪ እና ታሪኩ ታምራት ሲያስቆጥሩ የሞጆ ከተማን ብቸኛ ጎል ታመነ ቅባቱ አስቆጥሯል፡፡
ከጨዋታ በፊትና ፍፃሜው ላይ የኢትዮዽያ ህዝብ መዝሙር በመዘመር ለየት ያለ ድጋፍ የሚያሳዮት የወልቂጤ ከተማ ደጋፊዎች ባቱ ከተማን በበጭፈራ ሲያደምቋት አምሽተዋል፡፡
ረፋድ 04:00 ላይ በተደረጉት ጨዋታዎች አማራ ፖሊስ ደሴ ከተማን 4-2 ሲያሸንፍ አራዳ ክ/ከተማ ሚዛን አማንን 2-1 አሸንፏል፡፡
ውድድሩ ነገ ሲቀጥል በምድብ መ ባቱ ሜዳ ላይ በ08:00 ሽረ እንደስላሴ ከ ከለገጣፎ ከተማ ፤ 10:00 ላይ ሶሎዳ አድዋ ከ ዳባት ከተማ ይጫወታሉ፡፡ የምድብ ሐ ጨዋታዎች በሼር ሜዳ ሲደረጉ 08:00 ላይ መተሀራ ስኳር ከ ወሊሶ ከተማ ፤ አምበሪቾ ከ ካፋ ቡና የሚጫወቱ ይሆናል፡፡