የኦሬንጅ ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ አራተኛ የምድብ ጨዋታዎች ረቡዕ ሲደረጉ የደቡብ አፍሪካው ሻምፒዮን ማሜሎዲ ሰንዳውንስ እና አል አሃሊ ድል ቀንቷቸዋል፡፡ አሴክ ሚሞሳስ እና ዜስኮ ዩናይትድ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል፡፡
ከምድብ ሁለት ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ወደ ግማሽ ፍፃሜው ያለፈ የመጀመሪያው ክለብ ሆኗል፡፡ በሜዳው ሉካስ ሞርፒ ስታዲየም ዛማሌክስ ያስተናገዱት ብራዚሎቹ 1-0 ማሸነፍ ችለዋል፡፡ የዛማሌኩ አሊ ጋብር የፒርሲ ታኦን ክሮስ በራሱ ግብ ላይ አስቆጥሮ ዛማሌክን ለሽንፈት ዳርጎታል፡፡
ድሉን ተከትሎ ሰንዳውንስ በ9 ነጥብ የምድቡ አናት ላይ ሲቀመጥ አንድ ጨዋታ የሚቀረው ዛማሌክ በሶስት ነጥብ ሁለተኛ ነው፡፡ የዛማሌክን ሁለት ተከታታይ ሽንፈት ተከትሎ ኢኒምባ ወደ ግማሽ ፍፃሜው የማለፍ ተስፋው አንሰራርቷል፡፡
ሁለት ቀሪ ጨዋታ የሚቀረው ኢኒምባ ቀሪ ጨዋታዎቹን ማሸነፍ ከቻለ ሰንዳውንስን ተከትሎ ወደ ግማሽ ፍፃሜው ይገባል፡፡
የምድብ አንድ መሪው ዋይዳድ ካዛብላንካ በሜዳው እና ደጋፊው ፊት በአል አሃሊ ያልተጠበቀ ሽንፈትን ቀምሷል፡፡ አል አሃሊ ወደ ግማሽ ፍፃሜው የማለፍ ተስፋውን ባለመለመበት ጨዋታ 1-0 ማሸነፍ ሲችል ራሚ ራቢያ ለካይሮው ክለብ የድል ግቧን አስገኝቷል፡፡
በምድቡ ሌላ ጨዋታ አሴክ ሚሞሳስ አቢጃን ላይ ከዜስኮ ዩናይትድ ጋር 1-1 ተለያይቷል፡፡ ኢብራሂም ኮኔ አሴክን በ74ኛው ደቂቃ ቀዳሚ ሲያደርግ ጃክሰን ሙዋንዛ ከ4 ደቂቃዎች በኃላ ዜስኮን አቻ አድርጓል፡፡
ምድቡን ዋይዳድ በሰባት ነጥብ ሲመራ ዜስኮ በግብ ክፍያ ተበልጦ ሁለተኛ ነው፡፡ የመሪዎቹን ነጥብ መጣል ተከትሎ የ8 ግዜ የአፍሪካ ሻምፒዮኑ አል አሃሊ የነጥብ ልዩነቱን ወደ ሶስት ማጥበብ ችሏል፡፡
የረቡዕ ውጤቶች
አሴክ ሚሞሳስ (ኮትዲቯር) 1-1 ዜስኮ ዩናይትድ (ዛምቢያ)
ዋይዳድ አትሌቲክ ክለብ (ሞሮኮ) 0-1 አል አሃሊ (ግብፅ)
ማሜሎዲ ሰንዳውንስ (ደቡብ አፍሪካ) 1-0 ዛማሌክ (ግብፅ)