አዳማ ከተማ የቀድሞው የዋልያዎቹ ድንቅ አማካይ አዲስ ህንፃን በእጁ አስገብቷል፡፡ ለቀጣዮቹ 2 አመታት በክለቡ የሚያቆየውን ውልም ፈርሟል፡፡
ከሱዳኑ አል አህሊ ሸንዲ ጋር ያለውን ውል አቋርጦ ወደ ሃገር ቤት የተመለሰው አዲስ ስሙ ከተለያዩ ክለቦች ጋር ተያይዞ ቢቆይም ማረፊያው አዳማ ከተማ ሆኗል፡፡
በሼንዲ ከደሞዝ ጋር በተያያዘ አስቸጋሪ ጊዜያት ያሳለፈው አዲስ ህንፃ ወደ ሃገሩ ተመልሶ በመጫወቱ ደስተኛ መሆኑን ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግሯል፡፡
” በሱዳን ከነበረኝ አስቸጋሪ ጊዜ በኋላ ለአዳማ በመፈረሜ ደስተኛ ነኝ፡፡ የእግርኳስ ህይወቴን እንደአዲስ ለመጀመር ተነሳስቻለሁ” ብሏል፡፡
የአዲስ ዝውውር በክረምቱ ቡድኑን እያጠናከረ ለሚገኘው አዳማ ተጨማሪ ጥንካሬን የመፈጥር ይሆናል፡፡ አማካዩ የቡድኑ ስብስብ ለቻምፒዮንነት የሚያበቃ እንደሆነ ያምናል፡፡
” የአዳማ ስብስብ ጠንካራ ነው፡፡ በዚህ ክረምት የፈረምነው ተጫዋቾችም ለክለቡ ተጨማሪ ጥንካሬ እንፈጥራለን ብዬ አስባለሁ፡፡ በቀጣዩ የውድድር ዘመን ለሊጉ ዋንጫ እንፋለማለን” ብሏል፡፡
በኢትዮጵያ መድን በአጥቂነት የእግርኳስ ህይወቱን የጀመረው አዲስ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ ደደቢት እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ቁልፍ አማካይ መሆን ችሎ ነበር፡፡ በ2005 ክረምት ደደቢትን ለቆ ለሱዳኑ አል አህሊ ሼንዲ ከፈረመ በኋላ ከብሄራዊ ቡድን ጨዋታዎች ርቆ ቆይቷል፡፡