ፍሬው ሰለሞን ወደ ሀዋሳ?
የመከላከያው አማካይ ፍሬው ሰለሞን ከሀዋሳ ከተማ ጋር ድርድር እያደረገ እንደሆነ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡ ባለ ክህሎቱ አማካይ ቅዱስ ጊዮርገስ እንደሚፈርም ሲጠበቅ ቢቆይም ሀዋሳ ከተማ ሊጠልፈው እንደተዘጋጀ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ዮናታን ከበደን ከቀናቶች በፊት ለ2 አመታት ያስፈረመው ሀዋሳ ከተማ ተጨማሪ ተጫዋች ከውጭ ለማስፈረም እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሆነ ታውቋል፡፡
ሲዳማ ቡና አበበ እና ትርታዬን በይፋ አስፈረመ
ሲዳማ ቡና የአርባምንጭ ከተማዎቹ አበበ ጥላሁን እና ትርታዬ ደመቀን በይፋ ለ2 አመታት አስፈርሟል፡፡ ከሁለቱ ተጫዋቾች በተጨማሪ ከከፍተኛ ሊጉ ተጫዋቾች ማስፈረሙ ታውቋል፡፡
ሲዳማ ቡና የአማካዩ ፍፁም ተፈሪ እና በረከት አዲሱን ግልጋሎት ለተጨማሪ 2 አመታት ለማደስም ከስምምነት ላይ ደርሷል፡፡
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዮናስ ገረመው እና ሙሴ ገብረ ኪዳንን ለማስፈረም ተስማምቷል
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የውድድር ዘመኑን በድሬዳዋ ከተማ ሳለፈው ዮናስ ገረመውን ለማስፈረም ከስምምነት ደርሷል፡፡ ፋሲል ከተማ ለመፈረም ተቃርቦ የነበረው ዮናስ ንግድ ባንክን የተቀላቀለው በአንድ አመት ኮንትራት ነው፡፡
ንግድ ባንክ በለቀቃቸው ሁለት ግብ ጠባቂዎች ምትክ ሙሴ ገብረ ኪዳንን ከሀዲያ ሆሳዕና አስፈርሟል፡፡ ሙሴ በ2007 ከኢትዮጵያ ቡና ከለቀቀ በኋላ ይህን የውድድር አመት ለኤሌክትሪክ እና ለ ሀዲያ ሆሳዕና በመጫወት ማሳለፉ ይታወሳል፡፡
ንግድ ባንክ አምና ያስፈረመው ፌዞ ኢማኑኤልን ኮንትራት ያደሰ ሲሆን ፊሊፕ ዳውዚን የሚተካ ሁነኛ አጥቂ በገብያው ላይ እያሰሰ እንደሆነ ታውቋል፡፡
አርባምንጭ የተሾመ ታደሰ እና አማኑኤል ጎበናን ውል አድሷል
አርባምንጭ ከረጅም ድርድር በኋላ ተሾመ ታደሰ እና አማኑኤል ጎበና ለተጨማሪ አመታት ለማቆየት ውላቸውን አድሷል፡፡ ክለቡ በሁለቱ መፈረም እፎይታ ቢያገኝም የእንዳለ ከበደ ፣ ቢድግልኝ ኤልያስ እና ታደለ መንገሻ ውል እስካሁን እንዳልተራዘመ ታውቋል፡፡ ታደለ መንገሻ ውሉን እንዳደሰ ቢነገርም ከክለቡ ጋር እስካሁን መስማማት እንዳልቻለ ከክለቡ አካባቢ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ወላይታ ድቻ በመጪዎቹ ቀናት አዳዲስ ተጫዋቾችን እንደሚያስፈርም ይጠበቃል
ለምልመላ ዝዋይ የሚገኙት የወላይታ ድቻ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በመጪዎቹ ጥቂት ቀናት ትኩረታቸውን የሳቧቸው ተጫዋቾችን እንደሚያስፈርሙ ታውቋል፡፡ ወላይታ ድቻ የተከላካዩ ሙባረክ ሽኩርን ውል ለተጨማሪ 2 አመታት ማደሱም ተረጋግጧል
የድሬዳዋ ከተማ የአማካይ ክፍል እንደ አዲስ እየተገነባ ነው
አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ድሬዳዋ ከተማን በራሳቸው የአጨዋወት ስልት በመቃኘት ላይ ይገኛሉ፡፡ ዳዊት እስጢፋስ እና ዮናስ ገረመውን የለቀቁት ድሬዎች አሳምነው አንጀሎ ፣ ዘላለም ኢሳያስ ፣ ሚካኤል ለማ እና ሰለሞን ገብረመድህንን በማስፈረም የአማካይ መስመሩን አዲስ መልክ ሰጥተውታል፡፡
ፋሲል ከተማ ተጫዋቾችን ለማስፈረም የቦርድ ውሳኔ ይጠብቃል
ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ማደጉን ያረጋገጠው ፋሲል ከተማ የፕሪሚየር ሊጉ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾችን ለማስፈረም እንቅስቃሴ የጀመረ ሲሆን ክለቡ ለተጫዋች ዝውውር የሚያወጣው ገንዘብ ላይ ቦርዱ በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ሌላው ወደ ፕሪሚየር ሊግ ማደግ የተቃረበው ጅማ አባ ቡናም በሊጉ ትልቅ ስም ያላቸውን ተጫዋቾች ለማስፈረም የቦርዱን ውሳኔ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡