አሰልጣኝ ደረጄ በላይ ስለጅማ አባቡና ወደ ፕሪሚየር ሊግ ማደግ ይናገራሉ

ጅማ አባቡና ትላንት ወራቤ ላይ ከወራቤ ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርቶ በመውጣት 5 ጨዋታ እየቀረው ወደ ቀጣዩ አመት ፕሪሚየር ሊግ ማደጉን አረጋግጧል፡፡

ከኢትዮጵያ እግርኳስ ለረጅም ዘመናት ጠፍቶ የቆየው ጅማ አባ ቡና በ2006 በድጋሚ ሲመሰረት በ2009 ፕሪሚየር ሊግ ለመግባት ያስቀመጠውን ግብ አሳክቶ ወደ ሃገሪቱ ትልቅ ሊግ ማደግ ችሏል፡፡

ለቡድኑ ውጤታማነት ግንባር ቀደም ተጠቃሽ የሆኑት አሰልጣኝ ደረጄ በላይ በአመቱ ውስጥ እንዳሳዩት ወጥ አቋም ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ማደግ እንደሚገባቸው ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡

” ገና የዘንድሮው የውድድር ዘመን ሲጀምር ወደ ፕሪሚየር ሊግ እንምናድግ እርግጠኛ ነበርኩ፡፡ ገና አምስት ጨዋታ እየቀረን ፕሪሚየር ሊግ  መግባታችን የቡድናችንን ጥንካሬ እና ጥራት ያሳያል፡፡ ስለዚህ መግባታችን ይገባናል ” የሚሉት አሰልጣኝ ደረጄ አምና ለፕሪሚየርሊጉ ለማለፍ ተቃርበው የወደቁበት መንገድ ዘንድሮ በእልህ እንዲነሳሱ እንዳደረጋቸው ይናገራሉ፡፡

” የአምናው ሁኔታ በጣም ያስቆጫል፡፡ጫፍ ደርሰን በተሰራብን ደባ ነበር የወደቅነው፡፡  በእርሱ እልህ ተነሳስተን ጠንክረን በመስራታችን ፕሪሚየር ሊግ ገብተናል፡፡ ” ብለዋል፡፡

PicsArt_1470124483146

ዘንድሮ በከፍተኛ ሊጉ እንደ ጅማ አባ ቡና ወጥ አቋም ያሳየ ክለብ የለም ለማለት ያስደፍራል፡፡ 2 ጨዋታ ብቻ ከመሸነፉ ውጪ በሜዳው ሽንፈት አላስተናገደም፡፡ አሰልጣኝ ደረጄም ለውድድር ዘመኑ ያማረ ጉዞ ምክንያት ያሏቸውን ይገልጻሉ፡፡

” የቡድኑ ጥንካሬ ምንጭ በመጀመርያ ስብስባችን ነው፡፡ ተጫዋቾቹ ምርጥ ናቸው ፤ በጣም የሚገርም ዲሲፒሊን  አላቸው፡፡ ለልጆቼ ትልቅ ክብር አለኝ፡፡

ሁለተኛ የክለቡ ሀላፊዎች የሰጡኝ የስራ ነፃነት ነው፡፡ በስራዬ ጣልቃ አይገቡብኝም፡፡ ሌላው ደጋፊዎቻችን የሚገርሙ ናቸው፡፡ እነዚህ ነገሮች ተደማምረው ለዚህ በቅተናል፡፡ ”

ለኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን 6 ተጫዋቾችን ማስመረጥ የቻለው ጅማ አባ ቡና አመዛኞቹ ተጫዋቾች የሊጉ ልምድ የሌላቸው እንደመሆኑ ፕሪሚየር ሊጉን ለመላመድ በወጣት ስብስቡ ላይ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾችን እንደሚያክልበት አሰልጣኝ ደረጄ ገልፀዋል፡፡

” ቡድኑ ላይ የተወሰነ ለውጥ እናደርጋለን፡፡ ያነጋገርኳቸው ትልልቅ ተጫዋቾች አሉ፡፡ እነሱን ቡድናችን ላይ እናክላለን፡፡ እንደሚታወቀው አብዛኛዎቹ ወጣቶች ናቸው፡፡ የማሸነፍ ፍላጎታቸውና ጉልበታቸው የተለየ ነው፡፡ አብረው ሶስት አመት የቆዩ ናቸው፡፡ እነርሱ ላይ የተወሰኑ ልምድ ያላቸውን እንጨምርና በሚቀጥለው አመት በፕሪሚየር ሊጉ ላይ የመቆየት በሌላ አነጋገር ፕሪሚየር ሊጉን የመላመድ ጊዜ ይኖረናል፡፡ ከተሳካልን ደግሞ እስከ መጨረሻው እንሄዳለን፡፡ ” ብለዋል፡፡

አሰልጣኝ ደረጄ በመጨረሻም በጅማ አባ ቡና ስኬታማ ጊዜ እንዲያሳልፉ የረዷቸው የትዳር አጋራቸውን አመስግነዋል፡፡

“ለዚህ እንድበቃ ከጎኔ የነበረችው ባለቤቴን በጣም ነው የማመሰግናት፡፡ ምክንያቱም ከቤቴ ወጥቼ ውጭ ነው የምሰራው፡፡ ቤተሰቤን ተንከባክባ ችግር ቢፈጠር እንኳን ምንም አትነግረኝም ፤ ሙሉ ለሙሉ ሀሳቤን ጥቅልል አድርጌ ስራዬ ላይ ብቻ ትኩረት እንዳደርግ ትረዳኝ የነበረችውን ባለቤቴን አመሰግናለው፡፡ “

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *