ናይጄሪያዊው አጥቂ ፍሊፕ ዳውዝ ለኩዌቱ አል ናስር ክለብ በአንድ ዓመት ውል ለመጫወት ፊርማውን አውሏል፡፡
የተጫዋቹ ወኪል ዴቪድ በሻ በተደጋጋሚ ዳውዝ በኢትዮጵያ ውጪ ባሉ ክለቦች የመጫወት ፍላጎት እንዳለው ለሶከር ኢትዮጵያ መናገሩ ይታወሳል፡፡
ዳውዝ በኢትዮጵያ ቆይታው ለኤሌክትሪክ፣ ደደቢት እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጫውቶ ያሳለፈ ሲሆን በክረምቱ ዝውውር ስሙ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ተያይዞ ተነስቷል፡፡
እንደወኪሉ ዴቪድ ገለፃ ከሆነ ቡና የተጫዋቹን ግልጋሎት ለማግኘት ጥያቄ አቅርቦ የነበረ ቢሆንም ለሁለተኛ ጊዜ ወደ መካከለኛው ምስራቅ አምርቶ በኩዌት ሊግ ለሚወዳደረው አል ናስር ክለብ ፊርማውን አኑሯል፡፡
በቤኒን፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ኢትዮጵያ የእግርኳስ ህይወትን የመራው የፊት መስመር ተሰላፊው ለአል ናስር የፈረመነበትን የገንዘብ መጠን ወኪሉ ከመግለፅ ተቆጥቧል፡፡
አል ናስር እ.ኤ.አ በ1965 የተመሰረተ ሲሆን በ2015/16 የኩዌት ፕሪምየር ሊግ ውድድር ዘመን ወደ አንደኛ ዲቪዝዮን ወርዷል፡፡ ክለብ በውድድር ዘመኑ ከ24 ጨዋታዎች አንድ ጨዋታ ብቻ ሲያሸንፍ አራት ጨዋታችን በአቻ ውጤት ጨርሷል፡፡