አፍሪካ በሪዮ 2016፡ ናይጄሪያ ወደ ሩብ ፍፃሜ ያለፈች ብቸኛ የአፍሪካ ሀገር ሆናለች

የሪዮ ኦሎምፒክ የእግርኳስ የምድብ ጨዋታዎች ዕረቡ በተደረጉ ጨዋታዎች ተጠናቀዋል፡፡ አፍሪካን ከወከሉት ሶስት ሃገራት ናይጄሪያ ብቻ ሩብ ፍፃሜውን ስትቀላቀል አልጄሪያ እና ደቡብ አፍሪካ ከውድድሩ በጊዜ ተሰናብተዋል፡፡

ናይጄሪያን ከአትላንታ 1996 ኦሎምፒክ በኃላ ዳግም የወርቅ ሜዳሊያን ለማግኘት ግስጋሴዋን ቀጥላለች፡፡ አስቀድማ ማለፏዋን ያረጋገጠችው ናይጄሪያ በኮሎምቢያ 2-0 ሳኦ ፖሎ ላይ ተሸንፋለች፡፡ ሽንፈቱ ናይጄሪያን ምድብ ሁለትን በበላይት ከመጨረስ ባያግዳትም የአጥቂው ኦግሄንካሮ ኢቴቦ ጉዳት አግጥሞታል፡፡ የኮሎምቢያን የድል ግቦች ቴዮ ጉቴሬዝ እና ዶርላን ፖርቦ (ፍፁም ቅጣት ምት) አስገኝተዋል፡፡ አሰልጣኝ ሳምሶን ሲያሲያ ወደ ቀጣዩ ዙር አስቀግሞ ያለፈውን ቡድናቸው መካከል በመጨረሻው ጨዋታ በአብዛኛው ለተጠባባቂ ተጫዋቾች እድልን መስጠት መርጠዋል፡፡ ናይጄሪያ ቅዳሜ በሚደረገው የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ ዴንማርክን ትገጥማለች፡፡

በምድብ አንድ የምትገኘው ደቡብ አፍሪካ ከኢራቅ ጋር 1-1 ተለያይታለች፡፡ የአቻ ውጤቱ ሁለቱንም ሃገራት ከኦሎምፒኩ ውጪ አድርጓል፡፡ ግብ በማስቆጠር ቅድሚያውን የያዙት ደቡብ አፍሪካዎች ነበሩ ፤ በጊፍት ሞቱፓ አማካኝነት፡፡ የኢራቅን የአቻነት ግብ አምበሉ ሳአድ ሉአቢ ከመረብ አዋህዷል፡፡ ከምድቡ ብራዚል እና ዴንማርክ ተያይዘው አልፈዋል፡፡

አልጄሪያ ከፖርቹጋል ጋር 1 አቻ ተለያይታለች፡፡ ለአልጄርያ ግቡን ያስቆጠረው መሃመድ ቤንካቢሊያ ነው፡፡ ከምድብ አራት ፖርቹጋል እና ሆንዱራስ ወደ ሩብ ፍፃሜው ሲያልፉ አልጄሪያ እና አርጀንቲና ተሰናብተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *