የዳሽን ቢራ ህልውና ጉዳይ በቀጣዩ ሳምንት ይለይለታል

የዳሽን ቢራ ስፖርት ክለብ እንደ ክለብ የመቀጠሉ ወይም የመፍረሱ ጉዳይ በቅርቡ በሚጠራ ጋዜጣዊ መግለጫ ቁርጡ ይለያል ተብሏል፡፡

ዳሽን ቢራ ከፕሪሚየር ሊግ መውረዱን ተከትሎ የክለቡ እጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል በሚል የስፖርት ቤተሰቡን ሲያነጋግር መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ሶከር ኢትዮዽያ ለክለቡ ቅርበት ካላቸው ግለሰቦች በደረሳት መረጃ ዳሽን እንደ ክለብ የመቀጠሉ ነገር አክትሞለታል ተብሏል፡፡

በክለቡ የወደፊት እጣ ፈንታ ዙርያ የክለቡ ስራ አሰኪያጅ አቶ ልዑል ፍቃዱ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት የክለቡ ህልውናን የተፈታተነው በፌዴሬሽኑ የውሳኔ መዘግየት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

” ኢንተርናሽናል ተጨዋቾች ሲመጡ የፊፋ TMS መመዝገብ አለባቸው፡፡ ኢትዮዽያ ቡና ደግሞ ኤርሚያስ በለጠን ሳያስመዘግብ ከኛ ጋር በነበረው ጨዋታ አሰልፎታል፡፡ ይህንን መሰረት አድርገን ክስ ብናቀርብም እስካሁን ምላሽ አላገኘንም፡፡ “

አቶ ልኡል በዚህ ሳምንት ጋዜጣዊ መግለጫ በመስጠት ስለ ክለቡ ህልውና ይፋ እንደሚደረግም ተናግረዋል፡፡

” እንግዲህ ስለወደፊቱ ጠቅለል አድርገው የክለቡ ስራ አስፈፃሚ አባላት በሚቀጥለው ሳምንት ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት ዝግጁ ናቸው፡፡ ስለዚህ በቀጣይ ሳምንት ላይ የቡድኑ አጠቃላይ ህልውና ምን ይሆናል በሚለው ዙርያ መግለጫ ይሰጣሉ፡፡ “

አዲስ አበባ ላይ በሚሰጠው መግለጫ ክለቡ እንደሚፈርስ ይፋ ከተደረገ ከዚህ ቀደም በፕሪሚየር ሊጉ ተሳታፊ እንደነበሩት ትራንስ ኢትዮጵያ ፣ ጉና ንግድ ፣ ምድር ባቡር እና አርባምንጭ ጨርቃጨርቅ የመሳሰሉ ክለቦች ታሪክ ሆኖ ይቀራል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *