በኦሬንጅ ካፍ ኮንፌድሬሽን ካፕ ፉስ ራባት እና ኤቷል ደ ሳህል ከምድብ ሁለት ወደ ግማሽ ፍፃሜ ያለፉበትን ውጤት አስመዝግበዋል፡፡
ቱኒዚያ ውስጥ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ፉስ ራባት ከአል አሃሊ ትሪፖሊ 1-1 ሲለያዩ ኤቷል ደ ሳህል ካውካብ ማራካሽን 3-1 መርታት ችሏል፡፡
የ2015 ኮንፌድሬሽን ካፕ አሸናፊው ኤቷል ካውካብ ማራካሽን በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍፃሜው ማለፍ ችሏል፡፡ ሶስት ተከታታይ ሽንፈትን የቀመሰው የሞሮኮው ክለብም ከኮንፌድሬሽን ካፑ ውጪ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ መሃመድ ኤሃብ ሳክኒ (2) እና ሃምዛ ላሃማር የሶሱን ክለብ ሶስት ግቦች ከመረብ አዋህደዋል፡፡ የካውካብን የማስተዛዘኛ ግብ አህመድ ቻጉ በሁለተኛው አጋማሽ አስገኝቷል፡፡
ፉስ ራባት አስቀድሞ መውደቁን ካረጋገጠው አል አሃሊ ትሪፖሊ ጋር አቻ ተለያይቷል፡፡ የሞሮኮው ሻምፒዮን በምድብ መሪነቱ አሁን ቢቀጥልም ከሁለተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ኤቷል ደ ሳህል ጋር ያላቸው የነጥብ ልዩነት ወደ አንድ ዝቅ ብሏል፡፡ የሊቢያው ክለብ በምድብ ጨዋታው የመጀመሪያ ነጥቡን ማሳካት ችሏል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ እምብዛም ለተመልካች ማራኪ ባልነበረበት ጨዋታ ፉስ ራባት በየሱፋ ኔጂ ቀዳሚ ሲሆን ራቢ አል ላፊ የአቻነቷን ግብ ከመረብ አዋህዷል፡፡
የምድብ ሁለት አላፊ ቡድኖች በመታወቀቸው በስድስተኛው የምድብ መርሃ-ግብር ጨዋታዎች ፉስ ራባት እና ኤቷል ደ ሳሀል ምድቡን በመሪነት ለመጨረስ የሚያደርጉት ፉክክር ይጠበቃል፡፡
ዛሬ በምድብ አንድ ብቸኛው የምስራቅ አፍሪካ ተወካይ ያንግ አፍሪካንስ ዳሬ ሰላም ላይ ኤምኦ ቤጃያን ያስተናግዳል፡፡ በምድቡ መጨረሻ ደረጃ ላይ የሚገኘው ያንጋ የማል ተስፋው የደበዘዘ ሲሆን የአልጄሪያው ክለብ ወደ ግማሽ ፍፃሜው የሚያደርገውን ጉዞ ቀና ለማድረግ ሶስት ነጥብ ያስፈልገዋል፡፡ ካፍ ጨዋታውን እንዲመሩ ኢትዮጵያዊያን ዳኞችን መርጧል፡፡ ባምላክ ተሰማ፣ ክንዴ ሙሴ እና ተመስገን ሳሙኤል ጨዋታውን የሚመሩ ይሆናል፡፡
የዓርብ ውጤቶች
አል አሃሊ ትሪፖሊ (ሊቢያ) 1-1 ፋት ዩኒየን ስፖርት ራባት (ሞሮኮ)
ኤቷል ስፖርቲቭ ደ ሳህል (ቱኒዚያ) 3-1 ካውካብ አትሌቲክ ክለብ ማራካሽ (ሞሮኮ)
ቅዳሜ ነሃሴ 7/2008
16፡00 – ያንግ አፍሪካንስ (ታንዛኒያ) ከ ሞሊዲያ ኦሎምፒክ ቤጃያ (አልጄሪያ) (ናሽናል ስታዲየም)