አፍሪካ በሪዮ 2016፡ ናይጄሪያ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ስታልፍ ኢትዮ-ጀርመናዊው ግብ አስቆጥሯል

ናይጄሪያ በሪዮ ኦሎምፒክ ዴንማርክን በሩብ ፍፃሜው 2-0 በማሸነፍ ግስጋሴዋን ቀጥላለች፡፡ ድሪም ቲም በሚል ቅፅል ስም የሚጠራው የኦሎምፒክ ቡድኑ ዴንማርክ ላይ የጨዋታ የበላይነት የነበረው ሲሆን በአሳማኝ መልኩ የስካንዲቪያን ሃገሯን መርታት ችሏል፡፡

በአሬና ፎንቴ ኖቫ በተካሄደው ጨዋታ ያለ ኤቴቦ ኦግሄናካሮ ወደ ሜዳ የገባቸው ናይጄሪያ ከማሸነፍ ያገዳት ነገር አልነበረም፡፡

በቦነስ ክፍያ ምክንያት ከናይጄሪያ እግርኳስ ፌድሬሽን እና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር ግጭት ውስጥ ገብቶ የነበረው ብሄራዊ ቡድኑ በአምበሉ ጆን ኦቢ ሚካኤል ግብ በመጀመሪያ ግማሽ ቀዳሚ ሲሆን አሚኑ ኡማር በግንባሩ በመግጨት ሁለተኛውን ግብ አክሏል፡፡ ናይጄሪያ ከ2008 ቤጂንግ ኦሎምፒክ በኃላ ለግማሽ ፍፃሜው ቀርባለች፡፡

ናይጄሪያ በግማሽ ፍፃሜው ጀርመንን የምትገጥም ይሆናል፡፡ ጀርመን በሩብ ፍፃሜው ፖርቹጋልን 4-0 ረምርማለች፡፡ ለጀርመን አንዷን ግብ ከኢትዮጵያዊ አባት በጀመርመን የተወለደው የ21 ዓመቱ አጥቂ ዳቪ ስልኬ አስገኝቷል፡፡ ዳቪ በኦሎምፒኩ ሁለት ግቦች ማስቆጠር የቻለ ሲሆን ወደ ቦንደስሊጋው ላደገው ለአርቢ ላይፕዚሽ ይጫወታል፡፡ ብራዚል እና ሆንዱራስ ሌሎች ወደ ግማሽ ፍፃሜው ያለፉ ሃገራት ናቸው፡፡

PicsArt_1471161828314

በሴቶች እግርኳስ አንድም የአፍሪካ ቡድን ከምድብ ማለፍ አልቻለም፡፡ ወደ ግማሽ ፍፃሜው ብራዚል፣ ስዊድን፣ ካናዳ እና ጀርመን ማለፍ ችለዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *