በሪዮ ኦሎምፒክ የእግርኳስ ውድድር ናይጄሪያ በጀርመን በግማሽ ፍፃሜ 2-0 ተሸንፋ ወደ ፍፃሜ ሳታልፍ ቀርታለች፡፡ የጀርመን የመሃል ሜዳ እና የተከላካይ መስመር ጥንካሬ ናይጄሪያን ለማሸነፍ አሰችሏል፡፡ የናይጄሪያ ተጫዋቾችም በመጀመሪያው አጋማሽ የተዳከመ እንቅስቃሴ አሳይተዋል፡፡
የጀርመንን የመጀመሪያ ግብ ሉካስ ክሎስተርማን በ9ኛው ደቂቃ በጥሩ ሁኔታ ተመስርቶ የመጣ ኳስን ተጠቅሞ ከመረብ አዋህዷል፡፡ ከግቡ መቆጠር በኃላ ለረጅም ደቂቃዎች አቻ ለመሆን ሲጥሩ የነበሩት ናይጄሪያዎች አስደንጋጭ የሚባል ሙከራ ማድረግ ተስኗቸው ታይቷል፡፡ 89ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ወደ ናይጄሪያ ግብ ክልል መድረስ የቻሉት ጀርመኖች በኒልስ ፔተርሰን ግብ አሸናፊነታቸው አረጋግጠዋል፡፡ ለፔተርሰን ግብ መቆጠር የኢትዮ-ጀርመናዊው ዳቪ ስልኬ ሚና ይጠቀሳል፡፡ ዳቪ ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ግዜውን መጫወት ችሏል፡፡
ጀርመን በፍፃሜው ብራዚልን በማራካኛ ስታዲየም የምታሰተናግድ ይሆናል፡፡ ብራዚል ሆንዱራስ ላይ ግማሽ ደርዘን ግብ በማስቆጠር ለሁለተኛ ተከታታይ ግዜ ለፍፃሜ ቀርባለች፡፡ ናይጄሪያ ለነሃስ ሜዳሊያ ሆንዱራስን የምትገጥም ይሆናል፡፡
ጀርመን በሁለቱም ፆታ ለፍፃሜ ደርሳለች፡፡ በሴቶች እግርኳስ ጀርመን እና ስዊድን ለወርቅ ሜዳሊያው ይፋለማሉ፡፡