ናይጄሪያ በወንዶች እግርኳስ የነሃስ ሜዳሊያን አሸንፋለች፡፡ ለሶስተኛነት በተደረገው ጨዋታ ድሪም ቲም ተብሎ የሚጠራው የናይጄሪያ ኦሎምፒክ ብሄራዊ ቡድን በውድድሩ ሳይታሰብ አራቱ ውስጥ መግባት የቻሉትን ሆንዱራስን 3-2 ማሸነፍ ችለዋል፡፡
ከጀርመኑ ሽንፈት በተሻለ በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ መንቀሳቀስ የቻሉት ናይጄሪያዎች በሳዲቅ ኦማር ግብ 1-0 መምራት ችለዋል፡፡ ጆን ኦቢ ሚካኤል ለኦማር ግብ የሆነ ኳስ አመቻችቶ ማቀበል ትልቅ ሚናን ተውጥቷል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ አምበሉ ሚካኤል ወደ ግብ የላከውን ጠንካራ ምት የሆንዱራሱ ግብ ጠባቂ ሉዊስ ሎፔዝ ቢያመክነውም ከኳሱ በቅርበት የተገኘው አሚኑ ኦማር ሁለተኛውን ግብ ከመረብ አዋህዷል፡፡ በ60ኛው ደቂቃ ለጣሊያኑ ሮማ የሚጫወተው ሳዲቅ ኦማር የናይጄሪያ መሪነት ወደ 3 አስፍቷል፡፡
ጨዋታውን ለአብዛኛው ተመልካች የተጠናቀቀ ቢመስልም ሆንዱራስ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር ናይጄሪያ በጨዋታውን መጠናቀቂያ ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድራለች፡፡ የሆንዱራስ ከሽንፈት ያልታደጉ ሁለት ግቦች አንቶኒ ሎዛኖ እና ማርሴሎ ፔሬራ በግንባር በመግጨት አስቆጥረዋል፡፡
የናይጄሪያ ዋናው ብሄራዊ ቡደን ከአፍሪካ ዋንጫ ውጪ የሆነ ሲሆን ከ20 ዓመት እና ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድኖቹም ተመሳሳይ ዕጣ ደርሷቸዋል፡፡ የናይጄሪያ እግርኳስ ፌድሬሽን የፋይናንስ ቀውስ እና የተመሰቃቀለው አስተዳደር በወድድር ዓመቱን ናይጄሪያን እግርኳስ ቢያዳክምም የኦሎምፒክ ቡድኑ ውጤት ከማምጣጥ አልገታውም፡፡ በሪዮ በኦሎምፒክ ናይጄርያ ያገኘችው የመጀመሪያ ሜዳሊያ ሆኖም ተመዝግቧል፡፡
ናይጄሪያ በ1996 በአትላንታ ኦሎምፒክ እና ካሜሮን በ2000 በሲድኒ ኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ያሸነፉ ብቸኞቹ የአፍሪካ ሃገራት ናቸው፡፡