” ተጫዋቾቼ የሚችሉትን ሁሉ ሰጥተዋል” አስልጣኝ አጥናፉ አለሙ

በአፍሪካ ከ17 አመት ዋንጫ ማጣርያ አንደኛ ዙር ግብፅን በድምር ውጤት 5-2 ያሸነፉት ቀይ ቀበሮዎቹ ወደ ማዳጋስካሩ ውድድር ለማለፍ በመጨረሻው ዙር  ከማሊ ጋር ተፋጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች አሰልጣኝ አጥናፉ አለሙ ከትላንቱ ድል በኋላ ለጋዜጠኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ስለጨዋታው

ጥሩ ጨዋታ ነበር፡፡ በጣም ደስ ብሎናል፡፡ ተጫዋቾቹ የሚችሉትን ነገር በሙሉ አውጥተው ሰጥተዋል፡፡ ትንሽ ጉጉት ስለነበረባቸው በመጀመሪያው አጋማሽ ኳስ ተቆጣጥረን መጫወት አልቻልንም ነበር፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ልጆች የኢንተርናሽናል ጨዋታ እና ውድድር የልምድ የላቸውም፡፡ ገና ልጆች ስለሆኑ ጉጉት እና ከፍተኛ ጫና አለባቸው፡፡ ጫና ውስጥ ሆነው ጥሩ ባይጫወቱ አያስደንቀኝም፡፡ እነሱ (ግብጽ) ድካም ይታይባቸው ነበር፡፡ ይህም ለኛ ጥሩ ጎን ነበረው፡፡ ተጋጣሚያችን አንድ እድል ብቻ ነበር የነበረው ስለዚህም በጫና እንደሚጫወቱ እናውቅ ነበር፡፡ ኳስን ከተቆጣጠርክባቸው አሸንፈሃቸው መውጣት ትችላለህ፡፡ መልሶ ማጥቃትን አስበን ነበር ወደ ሜዳ የገባነው፡፡ ይህም ሲባል ተጠንቅቀን ተከላክለን በሂደት ለማጥቃት ነበር ሃሳባችን፡፡

ጥሩ ስለተንቀሳቀሱት ስለአቡበከር እና እሱባለው

አቡበከር የቤት ስራ ተሰቶት ነበር ወደ ሜዳ የገባው ምክንያቱም ጫላ እና ዳግማዊ እንደሚያዙ (ማርክ እንደሚደረጉ) አውቀን ነበር፡፡ ስለዚህ የመጨረሻ አጥቂ ያደረግነው አቡበከርን ነበር፡፡ እሱም ስራውን በሚገባ ሁኔታ ሰርቷል፡፡ እሱባለው የኛ ሮናልዲንሆ ጎቾ እንበለው፡፡ በሱ እንቅስቃሴ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ነገር ግን ወደ ቡድን እንቅስቃሴ መግባት አለበት፡፡

ስለቀጣይ ጨዋታ

እስቲ የነሱን ጨዋታ (የማሊ) መጀመሪያ እንየው፡፡ ለሁሉም ቡድን ጠንክረን ነው የምንዘጋጀው፡፡ ጥሩ ዝግጅት ይኖረናል ብዬ አስባለው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *