የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ከመስከረም 1 ጀምሮ በዩጋንዳ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የመጀመርያው የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ ዝግጅቱን ትላንት በድሬዳዋ ጀምሯል፡፡
በአሰልጣኝ መሰረት ማኒ የሚመሩት ሉሲዎቹ ባሳለፍነው ሳምንት የ31 ተጨዋቾች ምርጫ ይፋ ከተደረገ በኋላ ቅዳሜ ድሬዳዋ ገብተው መቀመጫቸውን ትሪያንግል ሆቴል በማድረግ ትላንት የመጀመርያ ልምምዳቸውን የሰሩ ሲሆን ዛሬም በድሬዳዋ ስታድየም ሁለተኛ ቀን ልምዳቸውን አከናውነዋል፡፡
ተጨዋቾቹ ከእረፍት እንደመመለሳቸው ወደ አካል ብቃታቸው እንዲመለሱ በማሰብ በቀን ሁለት ጊዜ ጠንከር ያለ ልምምድ ሰርተዋል፡፡
ይህ የልምምድ መርሃ ግብር ለአንድ ሳምንት የሚቀጥል ሲሆን የወዳጅነት ጨዋታዎች እና ቀለል ያሉ ልምምዶች የሚቀጥሉ ይሆናል፡፡
ከ31 ተጫዋቾች ስብስብ መካከል ሀብታም እሸቱ እና ቅድስት ቦጋለ ባጋጠማቸው የግል ጉዳይ ከቡድኑ ውጪ ሆነዋል፡፡
ሉሲዎቹ እስከ ጳጉሜ 1 ድረስ በድሬዳዋ የሚቆዩ ሲሆን 6 ተጨዋቾች ተቀንሰው 23 ተጫዋቾች ጳጉሜ 3 ቀን 2008 ወደ ዩጋንዳ ያመራሉ፡፡
ከዛሬው ልምምድ ፍጻሜ በኋላ ቡድኑን ወደ ሆቴል የሚያደርሰው ተሽከርካሪ ከ45 ደቂቃ በላይ በመዘግየቱ በቡድኑ አባላት ላይ መጉላላት የደረሰ ሲሆን በቀጣይ እንዲህ አይነት ክፍተቶች ሊታረሙ ይገባል መልክታችን ነው፡፡