የአፍሪካ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታ ወደ ናይሮቢ የቀናው መከላከያ በሊዮፓርድስ 2-0 ተሸንፏል፡፡
እንግዳው መከላከያ በ30ኛው ሰከንድ በሙሉአለም ጥላሁን አማካኝነት የመጀመርያ ሙከራውን ሲያደርግ የመጀመርያው ግብ እስኪቆጠርበት ድረስ ተመጣጣኝ ፉክክር አሳይቷል፡፡
መከላከያ ግብ ያስተናገደው ጨዋው በተጀመረ በ23ኛው ደቂቃ ሲሆን ማርቲን ኢምባላምባላ በግንባሩ በመግጨት ግቡን አስቆጥሯል፡፡ ከግቡ መቆጠር በኃላ ጫና የፈጠረው መከላከያ በ34ኛው ደቂቃ በሙሉአለም ጥላሁን አማካኝነት ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርጎ በግብ ጠባቂው ዋይክሊፍ ካሳያ ግብ ከመሆን ድኗል፡፡
በ43ኛው ደቂቃ ፖል ዌር ከመስመር ያሻገረውን ኳስ የኬንያ ፕሪሚየርሊግ ኮከብ ተጨዋቹ ጃኮብ ኬሊ አስቆጥሮ ሊዮፓርድስን በ2-0 መሪነት እረፍት እንዲወጡ አግዟል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ሙከራዎች ቢያደርጉም በግብ ጠባቂዎቹ ጥረት ግብ ሳይሆኑ ጨዋው በሊዮፓርድስ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ በጨዋው መከላከያ እንደተለመደው በኳስ ቁጥጥር የበላይ ቢሆንም የሊዮፓርድስን የመስመር አጨዋወት መቆጣጠር ሳይችል ወጥቷል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች ቀጣይ እሁድ በአዲስ አበባ ስታዲየም 10 ሰአት ላይ የመልስ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡
{jcomments on}