ሽመልስ በቀለ ልምምድ ጀምሯል
የፔትሮጄቱ አማካይ ሽመልስ በቀለ ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር ዛሬ የመጀመርያ ልምምዱን የሰራ ሲሆን እስካሁን ቡድኑን ያልተቀላቀለው የኦሶተርንድሱ ተከላካይ ዋሊድ አታ ብቻ ነው፡፡
የወዳጅነት ጨዋታ እጦት
ብሄራዊ ቡድኑ ዛሬ ረፋድ ላይ ባደረገው ልምምድ ለሁለት ተከፍሎ ጨዋታ ያደረገ ሲሆን እስካሁን ምንም አይነት የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን አለማድረጉ እንደከዚህ ቀደሙ አሉታዊ ተፅእኖ ሊያሳድርበት ይችላል ተብሏል፡፡
አብዱልከሪም መሃመድ በድጋሚ ጉዳት አጋጥሞታል
ብሄራዊ ቡድኑ በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ላይ ልምምድ ሲሰሩ አብዱልከሪም ቁርጭምጭሚቱ ላይ ጉዳት ያጋጠመው ሲሆን ለተከታታይ 3 ቀን ከልምምድ ርቋል፡፡ ለሺሰልሱ ጨዋታ የመድረሱ ነገርም አጠራጣሪ አድርጎታል፡፡ በኃይሉ አሰፋ ደግሞ በጡንቻው ላይ ጉዳት ደርሶበታል፡፡
ሀዋሳ ስታድየም
የሴካፋ ውድድሮችን ያስተናገደው አዲሱ ሀዋሳ ስታድየም በኢትዮዽያና ሲሸልስ መካከል የሚደረገውን ጨዋታ ያስተናገዳል፡፡ የመግቢያ ዋጋው ከ50-500 እንደሆነ ቢነገርም ከዋጋው ከፍ ማለት ጋር ተያይዞ የመግቢያው ዋጋ መጠን እንደ አስፈላጊነቱ ሊቀንስ እንደሚችል ታውቋል፡፡
ሲሸልስ
የሲሸልስ ብሄራዊ ቡድን ረቡዕ አዲስ አበባ ገብተው ወደ ሀዋሳ በማቅናት ማረፊያቸውን ሌዊ ሆቴል ያደርጋሉ፡፡
ዳኞች
ጨዋታውን የሚመሩት አራቱም ዳኞች ከዩጋንዳ ሲሆኑ ኮሚሽነሩ ከታንዛንያ ተመድቧል፡፡ እንደ ሲሸልስ ሁሉ ዳኞቹም ረቡዕ አአ ገብተው ወደ ሀዋሳ የሚያቀኑ ይሆናል፡፡