የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ከጣሊያኑ የስፖርት ትጥቅ አምራች ድርጅት ኤሪያ ጋር በትጥቅ አቅርቦት ላይ የአራት ዓመት ውል ፈርሟል፡፡ ውሉ በየዓመቱ የሚታደስ ሲሆን ኤሪያን ብቸኛው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የትጥቅ አቅራቢ ያደርገዋል፡፡
በጣሊያን የባህል ማዕከል በነበረው የትጥቅ ማስተዋወቅ ስነ-ስርዓት መጠናቀቅ በኃላ የእግርኳስ ፌድሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ወንድምኩን አላዩ የጋዜጠኞችን ጥያቆዎች መልሰዋል፡፡ እኛም ለአንባቢያን እንዲያመች አድርገን አቅርነበዋል፡፡
ስለስምምነቱ
” በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን እና ኤሪያ ስፖርት መካከል የተደረገው ስምምነት በየዓመቱ የሚታደስ ሆኖ ለአራት ዓመታት የሚቆይ ነው፡፡ ይህ ስምምነት ስድስት ቡድኖችን ከኦሎምፒክ ቡድኑ በስተቀር ያቅፋል፡፡ ይህ ስምምነት ዋሊያዎቹን፣ ሉሲን ከ20 ዓመት እና ከ17 ዓመት በታች ወንዶች እና የሴቶች ብሄራዊ ቡድን የሚያጠቃልል ነው፡፡ በዚህ ስምምነት መሰረት ፌድሬሽኑ በየዓመቱ የ90ሺ ዮሮ ትጥቅ ያገኛል ማለት ነው፡፡ ይህ ትጥቅ ያለምንም ክፍያ በነፃ የሚያገኘው ነው፡፡ ሃገር ውስጥ ሲገባ ከሚከፈለው ቀረጥ በስተቀር ሁሉንም ውጪ ማጓጓዣን ጨምሮ የሚሸፍነው ኤሪያ ነው፡፡ ሌሎች ተጨማሪ ትጥቆችን ደግሞ ፌድሬሽኑ በ20% ቅናሽ ተደርጎለት የ50ሺ ዮሮ ትጥቅ ይገዛል ማለት ነው፡፡
ስለትጥቆቹ ዝርዝር
የትጥቆቹ ዓይነት በጣም ብዙ ነው፡፡ እያንዳንዳቸው በዋጋቸው ተዘርዝረው ነው፡፡ ለምሳሌ መለያ ልብስን ስንመለከት በሜዳችን ላይ ስንጫወት 120 መለያዎች በዓመት ድርጅቱ ያቀርባል፡፡ ከሜዳው ውጪም ሲጫወት 120 እንዲሁም የመጠባበቂያ 120 መለያዎች በዓመት ያቀርባል፡፡ ቲሸርቶችን እና ቁምጣዎች ደግሞ 60 ያቀርባል፡፡ ሶስት ዓይነት ቲሸርቶች ናቸው፡፡ በተመሳሳይ ቱታዎችን ከነሲከራቸው (40 ጫማዎች) እና ቦርሳዎችን ያቀርባል፡፡ ለግብ ጠባቂዎቹም ሙሉ መለያ ከነጓንታቸው በየዓመቱ ያቀርባል፡፡ በስፖንሰርሺፕ ስምምነቶች ውስጥ በአብዛኛው ያልተካተተው ነገር ግን እኛ ያካተትነው የመጫወቻ ጫማ ነው፡፡ በእኛ ሃገር ጥራቱን የጠበቀ ጫማ ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ከድርጅቱ ጋር ባደረግነው ድርድር ቢያንስ በአንድ ጨዋታ አርባ ጫማዎችን እንዲያቀርቡልን ተስማምተናል፡፡ ለሲሸልሱ ጨዋታ ሲባል ብቻ 40 ልዩ ታኬታዎችን ድርጅቱ አቅርቧል፡፡ ሌሎች ትናንሽ ነገሮችን ውሉ አካቷል ለምሳሌ የአርምባንድ እና የውሃ መጠጫው ይጠቀሳል፡፡ 46 የተለያዩ ቁሳቁሶች ናቸው በውሉ ላይ የተዘረዘሩት፡፡
የብሄራዊ ቡድን ውጤት በውሉ ላይ ስላለው ተፅዕኖ
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ውጤት ባመጣ ቁጥር ስምምነቱ በዛው ልክ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ውሉ የአራት ዓመት ቢሆንም በየዓመቱ እንዲታደስ የተደረገውም ለዚሁ ነው፡፡ የብሄራዊ ቡድኖቹ ደረጃ እየጨመረ ሲሄድ በዛው ልክ የምናቀርባቸው ጥያቄዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ አሁን ባለን ደረጃ ላይ ተጨማሪ ገንዘብ እና መኪናን ለመጠየቅ አቅሙ አነሰን፡፡ ሴካፋ ላይ የሴቶች ብሄራዊ ቡድን ውጤት ቢያመጣ የስፖንሰርሺፕ ደረጃው ካለበት በ10% ይጨምራል፡፡
ኤሪያ በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ የሚኖረው አስተዋፅኦ
እግርኳሱን የመደገፍ ፍላጎት አላቸው፡፡ ለምሳሌ ከጣሊያን አሰልጣኞችን አምጥተው እዚህ እንዲያግዙ እና እንዲያማክሩ የማድረግ ፍላጎት አላቸው፡፡ በብሄራዊ ቡድን ደረጃ እኛ የምንስማማ ከሆነ የጣሊያን የሰውነት ማጎልመሻ አሰልጣኞች አምጥተው መርዳት ይፈልጋሉ፡፡ ቡድኑ ውጤታማ የሆነ ቁጥር የነሱም ገበያ እየጨመረ ነው የሚሄደው፡፡ ይህንን በአይስላንድ አይተውታል፡፡ የአይስላንድ ብሄራዊ ቡድን እያሸነፈ ሲሄድ አንድ የአይስላንድ መለያ እስከ 80 ዮሮ ድረስ ተሽጧል፡፡
ለደጋፊዎች የሚቀርቡ መለያዎች
የደጋፊዎች መለያ በተመለከተ ኤሪያ ለራሱን ሱቅ ኢትዮጵያ ውስጥ ይከፍታል፡፡ ለአሁን ግን የተወሰነ ያመጡቸው ወደ 1000 የሚሆኑ መለያዎች አሉ፡፡ ህዝቡ ለእግርኳስ ያለውን ፍቅር እና የገበያውን ሁኔታ ስለተረጉት የራሳቸውን ሱቅ የሚከፍቱ ይሆናል፡፡ መለያዎች ተሽጠው ከሚገኘው ገቢም እግርኳሱን እንደሚደግፉ ይጠበቃል፡፡