ሰርቢያዊው ሰርዮቪች ሚቾ ሚሉቲን ዩጋንዳን ከ39 ዓመታት በኃላ የአፍሪካ ዋንጫ እንድታገኝ አስችሏል፡፡ ሚቾ ወደ አፍሪካ ከመጣ 15 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን በዩጋንዳ፣ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ሱዳን ክለቦች ማሰልጠን ችሏል፡፡ በብሄራዊ ቡደን ደረጀ ሩዋንዳ እና ዩጋንዳን መርቷል፡፡
ሚቾ ክሬንሶቹ ኮሞሮስን በፋሩክ ሚያ ግብ 1-0 ካሸነፉ በኃላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
ኮሞሮስን አሸንፏችሁ አልፋኋል፡፡ የጨዋታ የበላይነት እና ብዙ የግብ ሙከራዎችን በመከላከል በተጠመደው ኮሞሮስ ላይ አድርጓችኋል፡፡ ጨዋታውን እንዴት አየኸው?
“የጨዋታ የበላይነት ነበረን፡፡ ግብ የማግባት ዕድሎችን አምክነናል፡፡ በእግርኳስ የምታገኛቸውን እድሎች የምታመክን ከሆነ ልትጎዳ ትችላለህ፡፡ እኛ ግን ይህንን አልፈናል፡፡ ትልቁ እና ዋናው ነገር ይህ ነው፡፡”
አፍሪካ እግርኳስ መለዋወጡን ቀጥሏል፡፡ ኮሞሮስም ቀላል ተጋጣሚ አልነበረችም. . .
“የአፍሪካ እግርኳስ ምህዳር እየተለወጠ ነው፡፡ ተጋጣሚያችንን ኮሞሮስን ተመልከት፡፡ ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾችን የያዘ ቡድን ነው፡፡ በህንድ ውቅያኖስ ከሚገኙ ደሴቶች የተሻሉ እና ምርጦች ናቸው፡፡ ከማዳጋስካር፣ ሞሪሺየስ እና ሲሸልስ በጣም የተሻሉ ናቸው፡፡ ተጫዋቾቹን ከተመለከትን እንደሆነ ጥሩ ብቃት እና አቅም ያለቸው ናቸው፡፡ ግብ ጠባቂው አሊ አህመድ ለፈረንሳይ ከ21 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን ከቶትንሃሙ ሁጎ ሎሪስ በፊት ግብ ጠባቂ ነበር፡፡ ከሪቤሪ እና ቤንዜሜ ጋር የተጫወተ ነው፡፡ አሁን በቱርክ ካይዘርስፖር ነው የሚጫወተው፡፡ ሌሎችም መጥቀስ ይቻላል እንደ አጥቂው ቤን ፋራዱኦ መሃመድ፡፡ መሃመድ አርሰናልን በቻምፒየንስ ሊጉ ኤምሬትስ ላይ ያሸነፈው የግሪኩ ኦሎምፒያኮስ ተጫዋች ነው፡፡”
በታህሳስ ወር በሴካፋ ሲኒየር ዋንጫ የተገናኘን ጊዜ አንድ የምስራቅ አፍሪካ እግርኳስ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ስኬታማ ነው የሚባለው ወደ አፍሪካ ዋንጫ ወይም ወደ ሌላ ትልቅ ውድድር ሃገሩን ሲያሳልፍ ነው ብለህ ነበር፡፡ አሁን ላይ ሚቾ ስኬታማ ነው?
“አሁን ላይ በአፍሪካ እግርኳስ ባለታሪክ ሆኛለው፡፡ በ15 ዓመታት ቆይታዬ 12 የሊግ እና የጥሎ ማለፍ ዋንጫዎችን በ4 የተለያዩ ሃገራት ማሸነፍ ችያለው፡፡ 3 ግዜ የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌድሬሽን ካፕ የግማሽ ፍፃሜ ተፋላሚ ነበርኩ፡፡ የሴካፋ ክለብ ዋንጫ እና ሲኒየር ቻሌንጅ ካፑ ማሸነፍ ችያለው፡፡ 2 ግዜ የቻን ተሳትፎን ማረጋገጥ ችያለው፡፡ በዛ ላይ ዩጋንዳን ከ39 አመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ መልሻለው፡፡ በተለይ ይህ ውጤት ለእኔ ትልቁ ስኬቴ ነው፡፡ ምንም እንኳን ወርሃዊ ደሞዝ እየተከፈለኝ ቢሆንም ለህልሜ ሰርቼ ውጤትን ማምጣት ችያለው፡፡”
ለዩጋንዳ ብሄራዊ ቡድን ይህንን ውጤት የማምጣት ዋናው ምክንያት ምን ይሆን?
“ለዩጋንዳ ስኬታ መሰረት አድርጌ የምወስዳቸው የፌድሬሽኑን ፕሬዝደንት ኢንጂነር ሞሰስ ማጎጎ እና ዋና ፀሃፊውን ዋትሰን ናቸው፡፡ ሁለቱም በእኔ ላይ ትልቅ አመኔታ ነበራቸው፡፡ ሁለቱንም ቪላ በነበርኩበት ወቅት ነበር የማውቃቸው እና ውጤት እንደማመጣ ያውቁ ነበር፡፡”