የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ አማካይ ቢንያም በላይ በጀርመን የተሳካ የሙከራ ጊዜ አድርጎ እንደመጣ ለሶከር ኢትዮዽያ ተናግሯል፡፡
ቢንያም በጀርመን የሙከራ ጊዜ እንዲያሳልፍ ያመቻቹለት የፌዴሬሽኑ የቴክኒክ አማካሪ ዮአኪም ፊከር ሲሆኑ አንድ ወር ከሃያ ቀናት የሙከራ ጊዜ አሳልፏል፡፡
ቢንያም በጀርመን ስለነበረው ቆይታ እንዲህ በማለት ያብራራል፡፡
“እንደሄድኩ ቀጥታ ወደ ሙከራ አልገባሁም፡፡ አዲስ አበባ በግሌ ስሰራ ጉዳት አጋጥሞኝ ስለነበር ለአንድ ሳምንት ጉዳቴን አስታምሜ ነው ወደ ሙከራው የገባሁት፡፡ መጀመርያ ለአስራ አምስት ቀን የቆየሁት ቦሩሲያ ሞንችላግባህ ሲሆን እዛም ከሁለተኛው ቡድን ጋር ጥሩ የሙከራ ጊዜ ነበረኝ፡፡ እነሱም በእኔ ደስተኛ እንደሆኑ እና ለዋናው ቡድን ሊያስፈርሙኝ እንደሚፈልጉ ነገረውኝ ነበር፡፡ ሆኖም ይህ ለኔ ከባድ ነው ብዬ በማሰብ ለሁለተኛ ሙከራ ወደ ኤፍሲ ኮለኝ አምርቼ ነበር፡፡ እዛም ጥሩ ጊዜ ቢኖረኝም ተመሳሳይ ጥያቄ ነው ያቀረቡልኝ፡፡ በተመሳሳይ ሌሎች ክለቦች ጥያቄ ቀርቦልኝ የነበረ ቢሆንም የቪዛዬ ቀን በማለቁ ወደ ሀገሬ ተመልሻለው ” ብሏል፡፡
ቢንያም የበርካታ ክለቦች ፍላጎትን ወደ ኀላ ብሎ ያልፈረመበት ምክንያት በዋናው ቡድን በፍጥነት ሰብሮ ለመግባት አዳጋች እንደሆነ በማመኑ እንደሆነ ይገልፃል
” በጀርመን እግርኳስ ህግ መሰረት ከጀርመን ዜጋ ውጪ የሚመጡ ተጨዋቾችን በቀጥታ ወደ ዋናው ቡድን ነው የሚያስገቡት፡፡ ይህ ደግሞ ለኔ በጣም ከባድ ነው፡፡ በሃገሪቱ ከፍተኛው ሊግ ውስጥ አሁን ባለኝ ወቅታዊ አቋም ተፈካካሪ ሆኖ የቋሚነት እድል ለማግኘት ከባድ ከመሆኑ የተነሳ ለብዙ ጊዜያት ተጠባባቂ ወንበር ላይ ልቀመጥ እችላለሁ፡፡ ይህ ደግሞ አቋሜን ጠብቄ ለመዝለቅ የሚከብደኝ በመሆኑ ለመፈረም አልቻልኩም፡፡ ሌሎች ሀገሮች ማለትም እንደ አልባንያ እና ቤልጅየም የቀረበልኝ ጥያቄ ነበር ፤ ሆኖም የኔ ቪዛ ቀነ-ገደቡ ያለቀ ከመሆኑ በተጨማሪ የዝውውር መስኮቱ ስለተዘጋ ዝውውር ለማድረግ የግድ የጥር ወር መስኮት መከፈትን መጠበቅ ይኖርብኛል” የሚለው ቢንያም በጥር ወር ለአንድ የአውሮፓ ክለብ ፊርማውን እንደሚያኖር ተማምኗል፡፡
” አሁን ለበአል ከቤተሰቤ ጋር በድሬደዋ ከተማ እገኛለው፡፡ በአዲሱ የውድድር ዘመን ከክለቤ ጋር ያልተጠናቀቀ ኮንትራት ስላለኝ ኢትዮዽያ ንግድ ባንክን የማገለግል ይሆናል፡፡ ጥር ወር ላይ ከወኪሌ ጋር ተነጋግሬ ለቀጣይ እግር ኳስ ህይወቴ ወደሚጠቅመኝ ክለብ ፊርማዬን አኖራለሁ” ሲል ሀሳቡን አጠቃሏል፡፡
[socialpoll id=”2385802″]
[socialpoll id=”2385807″]