ጌታነህ ከበደ ወደ ደደቢት ተመለሰ

በክረምቱ ማረፊያው የት እንደሚሆን አነጋጋሪ ከሆኑት ተጫዋቾች አንዱ የሆነው ጌታነህ ከበደ በመጨረሻም ወደ ደደቢት የሚመልሰውን ዝውውር አድርጓል፡፡

የውድድር ዘመኑን በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ፕሪቶርያ በውሰት ያሳለፈው ጌታነህ ከቢድቬትስ ዊትስ ጋር ከተለያየ በኋላ ከሌሎች የደቡብ አፍሪካ ክለቦች እና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ስሙ ቢያያዝም ወደ ደደቢት ተመልሷል፡፡ ጌታነህ ለ2 የውድድር ዘመናት ለደደቢት ለመጫወት የተስማማ ሲሆን የኮንትራት ዋጋው ምን ያህል እንደሆነ አልተገለፀም፡፡

በ2001 ክረምት ደቡብ ፖሊስን ለቆ ወደ ደደቢት ያመራው ጌታነህ በ3 የውድድር ዘመናት የክለቡ ቆይታው 2 ጊዜ የሊጉ ከፍተኛ ግብ አግቢ ሆኖ ሲያጠናቅቅ በ2005 ቡድኑን በአምበልነት በመምራት ለሊግ ቻምፒዮንነት ማብቃቱ ይታወሳል፡፡ በዚህ የውድድር ዘመንም ለብሄራዊ ቡድኑ 6 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ግቦችን ጨምሮ 8 ግቦችን ከመረብ አሳርፏል፡፡

የጌታነህ መመለስ ተከትሎ በ2005 የውድድር ዘመን በጣምራ 43 ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ በሊጉ ከታዩ አስፈሪ ጥምረቶች አንዱ የነበረው የጌታነህ ከበደ-ዳዊት ፍቃዱ ጥምረትን በድጋሚ የምንመለከትበት እድል ፈጥሮልናል፡፡

ደደቢት ከአምናው ያልተሳካ የዝውውር ገበያ ትምህርት የወሰደ ይመስላል፡፡ አስራት መገርሳ ፣ ጌታነህ ከበደ እና ኤፍሬም አሻሞን በማስፈረምም የስብስቡን ጥራት ከፍ አድርጓል፡፡



[socialpoll id=”2385802″]

[socialpoll id=”2385807″]

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *