የወጣቶች እግርኳስ | 05-01-2009
የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን ወደ ማዳጋስካሩ የ2017 የአፍሪካ ከ17 አመት በታች ዋንጫ ለማለፍ ሁለተኛ ማጣርያውን ከማሊ ጋር ያደርጋል፡፡
በመጀመርያው ዙር ማጣሪያ ግብፅን በድምር ውጤት በመርታት ወደ መጨረሻው ዙር ያለፈው ታዳጊ ቡድናችን ከ10 ቀናት በላይ በሀዋሳ ዝግጅቱን ሲያደርግ የቆየ ሲሆን 20 ተጨዋቾችን 5 የአሰልጣኞች ቡድን አባላት እና አንድ የቡድን መሪ በአጠቃላይ 26 የልኡካን ቡድን በመያዝ ነገ ጠዋት 03:00 ወደ ማሊ ይበራል፡፡
ብሄራዊ ቡድኑ ከ5 ሰአት በረራ በኋላ ማሊ የሚገባ ሲሆን አመሻሹ ላይ በባማኮ የመጀመርያ ልምምዱን የሚሰራ ይሆናል፡፡
በአጠቃላይ በቡድኑ ላይ ከፍተኛ ተነሳሽነትና ፍላጎት የሚታይ ሲሆን ጨዋታውን በድል ለመወጣት እንደተዘጋጁ የቡድኑ አባላት ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ እና ማሊ ከ17 አመት በታች ብሄራዊ ቡድኖች በመጪው እሁድ በባማኮ ሞዲቦ ኬይታ ስታድየም ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ሲሆን ጋናዊያን ዳኞች ጨዋታውን ይመሩታል፡፡
ሶከር ኢትዮጵያ ከአሰልጣኙና ተጫዋቾቹ ጋር ያደረገችውን ቆይታ ነገ ይዘን የምንቀርብ ይሆናል፡፡