አብነት ገብረመስቀል በካፍ ጉባኤ ንግግር አደረጉ

የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ሊቀመንበር አቶ አብነት ገ/መስቀል ፣ የፊፋ ፕሬዚዳንት ሴፍ ብላተር እና ኢሳ ሀያቱ የተሳተፉበት በአፍሪካ በአይነቱ የመጀመሪያው የሆነው የእግር ኳስ ክለቦች የምክክር ጉባኤ በደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን ከተማ ተካሄደ፡፡

ለሁለት ቀናት በተካሄደው በዚህ ጉባኤ የአፍሪካ ምርጥ የተሰኙ 37 ክለቦች የተሳተፉ ሲሆን ኢትዮጵያዊው ቅ/ጊዮርጊስም በፕሬዚዳንቱ አቶ አብነት ገ/መስቀል ተወክሏል ፡፡ በጉባኤው የክለቦች ፕሮፌሽናል ላይሰንስ፣ የጅምናዚየምና የውድድር ሜዳዎች ጥራት፣ የቲቪ ራይትና ታዳጊ ወጣቶችን እንዴት ማፍራት ይቻላል የሚለው ነጥቦች ተነስተዋል፡፡

ጉባኤው በአፍሪካ እያደገ በመጣው ፕሮፌሽናሊዝም ዙሪያ ጥልቅ ውይይት ከማድረጉም በላይ በየሀገሩ የሚገኙ ክለቦች የቢሮአቸው አደረጃጀት ዘመናዊና ፕሮፌሽናል የሆነ ማኔጅመንት እንዲኖረው የሚያስችል ጥናትም ቀርቦአል፣ ክለቦች ከስፖንሰር ሺፕ ጋር የሚያደርጉት ግንኙነት በዘፈቀደ ሳይሆን በጥናትና በዶክመንት የተደገፈ መሆን እንደለበትም ተነስቶአል፡፡

በጉባኤው ላይ ታዳጊዎችን እንዴት ማፍራት ይቻላል? በሚለው ዙሪያ ንግግር ያደረጉት አቶ አብነት ገ/ መስቀል ‹‹ ተተኪ ታዳጊዎችን ለማፍራት የተሟላ ፋሲሊቲ ያስፈልጋል፣ ለዚህ ስኬት ደግሞ ክለቦች፣ መንግስት፣ ጤና ጥበቃ፣ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ፌዴሬሽን፣ ካፍና ፊፋን በአንድነት ያጣመረ መሰረታዊ የስልጠና መርሀ ግብር መዘርጋት ይኖርበታል ›› በማለት ተናግረዋል፡፡

ተተኪ ተጫዋች ለማግኘት የውድድር አድማስንም ማስፋት ወሳኝ መሆኑን ያስቀመጡት አቶ አብነት በሀገራችን የተለመደው ብሄራዊ ሊግና ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ብቻ መሆኑ ተተኪዎችን ለማግኘትና አማራጭ ለማየት አስቸጋሪ እንዳደረገው ገልጸዋል፡፡

‹‹ከመደበኛ ውድድሮች በተጓዳኝ ታዳጊዎችን ማዕከል ያደረገ በስፖንሰሮች ውድሮችን በማድረግ ከሚገኘው ገቢ በተጨማሪ ለመታየት የሚጓጉ ብቃት ያላቸውን ተጫዋቾች ማፈራት ይቻላል፣ ማዘጋጃ ቤትም በተለያዩ የኮንዶሚኒየም ስፍራዎች የተወሰነ ሜዳ በመከለል ሜዳ ቢያዘጋጅ ለውጦችን ማየት እንችላለን ነገር ግን ይህን ማሟላት ባልቻልንበት ሁኔታ ዘላቂ ውጤት መጠበቅና ተተኪዎችን አድኖ ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ነው ብለዋል፡፡ ባለሀብቶች ለስፖርቱ እድገት ሜዳ ለመገንባትና ታዳጊ ፕሮጀክት ፋሲሊቲዎችን ለማስተካከል ለሚስገቡዋቸው እቃዎች መንግስት ከቀረጥ ነፃ ትብብር በማድረግ ሊያበረታታ ይገባዋል ››

ከፊፋው ፕሬዚዳንት ሴፕ ብላተር እና ኢሳ ሀያቱ ጋር በቅርብ በመገናኘት በተለያዩ ነጥቦች ዙሪያ የተወያዩ ሲሆን ባላቸው አቅም የኢትዮጵያ እግርኳስን ለማሳደግ ከካፍ እና ፊፋ ጋር በቅርበት እንዲሰሩ ሴፕ ብላተር ጠይቀዋል››

አቶ አብነት ገ/መስቀል ‹‹ የእኔ ልፋትና ድካም ለአንድ ቅ/ጊዮርጊስ ክለብ ብቻ ሳይሆን ለሀገሬም ነው፣ ሀገሬን በጣም የምወድ ሰው ነኝ እናም አለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ተቀብለን በጋራ በመሆን የሀገራችንን እግር ኳስ ለማሳደግ መስራት ይኖርብናል፣ የሀገር ውስጥ ክለቦችም እርባና ቢስ የሆነውን እንኪ ሰላምቲያ ትተን ለጋራ ጭቅማችን በጋራ በመሆን በቲቪ ራይት የሚገኝን ጥቅም ለማስከበር በቁርጠኝነት መስራት ይጠበቅብናል›› ሲሉ ንግግራቸውን አገባደዋል፡፡

ምንጭ ሊግ ስፖርት ጋዜጣ via ድሬቲዩብ

{jcomments on}