የወጣቶች እግርኳስ| 07-01-2009
የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን ማዳጋስካር ለምታስተናግደው የቶታል 2017 አፍሪካ ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ ለማለፍ በሚደረገው የመጨረሻ ዙር ማጣርያ የማሊ አቻውን ባማኮ ላይ ለምግጠም ወደ ስፍራው ተጉዟል፡፡ አሰልጣኝ አጥናፉ አለሙ ቀይ ቀበሮዎቹን እየመሩ ግብፅን በአጠቃላይ ውጤት 5-2 ያሸነፉ ሲሆን ለማሊው ጨዋታም በቂ ዝግጅት እንዳደረጉ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡
“ከነሃሴ 29 – መስከረም 4 ለተከታታይ 8 ቀናት ሃዋሳ ላይ ጥሩ ዝግጅት አድርገናል፡፡ ይህ በአካልም በአዕምሮም እንዲሁም በቴክኒካል እና በታክቲካል ረገድ ያሉትን ስራዎች በቡድኑ ላይ ለውድድር በሚያበቃ የእንቅስቃሴ ሂደት ውስጥ ጥሩ ዝግጅት አድርገናል፡፡” ይላሉ፡፡
ቀይ ቀበሮዎቹ በስብስባቸው ውስጥ አዳዲስ ተጫዋቾችን ለማካተት ባደረጉት ጥረት የኤምአርአይ ዕድሜ ምርመራ መውደቃቸው አሰልጠኝ አጥናፉ እንደችግር ጠቅሰዋል፡፡ “በሚገርም ደረጃ ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾችን አግኝተን ነበር፡፡ ለምሳሌ እስራኤል ሸጎሌ የሚባል የአርባምንጭ ልጅ በጣም ጥሩ ተጫዋች ነው፡፡ በቡድኑ ውስጥ ቢካተት ቡድናችን ጠንካራ ይሆን ነበር ነገር ግን በዕድሜ ችግር ወድቋል፡፡ ፋሲል አለማየሁ የሚባል ልጅ ከዲላ አግኝተናል፡፡ ጥሩ ልጅ ነው የኤምአርአይ ውጤቱም አሳልፎታል፡፡ የኤምአርአይ ውጤታቸው አይተን አራት ልጆች ግብፅን የገጠመው ቡድን ላይ አካተናል፡፡”
ቺሊ ባስተናገደችው የፊፋ የዓለም ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ የፍፃሜ ተፋላሚ የነበረችው ማሊ በቅርብ አመታት ውስጥ ጥሩ ቡድን እየገነባች እንደሆነ አሰልጣኝ አጥናፉ ጨምሮ ገልፀዋል፡፡ “ማሊን እንግዲህ በመረጃ ደረጃ ከ13 ዓመት እድሜያቸው ጀምሮ አብረው የቆዩ ተጫዋቾችን የያዘ ቡድን ነው፡፡ እንዲሁም የኛ ከ20 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን ከማሊ ጋር ለአቋም መለኪያ ሲጫወት የማሊው ከ20 ዓመት በታች ቡድንም እንደዛው ከ15 ዓመታቸው ጀምሮ አንድ ላይ የነበሩ ናቸው፡፡ በወጣቶች ደረጃ ምን ያህል ወረድ ብለው በጠንካራ ሁኔታ እንደሚሰሩ መረጀ አግኝተናል፡፡ ብዙ ግዜ ባንዘጋጅበትም የህክምናው እና እድሜው ነገር ኖሮ እግርኳስ በጥራት ደረጃ ላይ ስለሚሰራ ነው እንጂ እኛም ጋር ከተሰራ በጣም ጥሩ ተፎካካሪ መሆን የሚችሉ ወጣቶች አጋጥመውናል፡፡ የማሊ የአጨዋወት ዘይቤያቸው ከ20 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድናቸው የተለየ ሊሆን አይችልም፡፡ አብዛኛውን ግዜ ረጃጅም ኳሶችን እና በመስመር እንደሚጫወቱ መረጃውን አግኝተናል፡፡ ሙሉ የቻድ ጨዋታቸውን ማግኘት ባንችልም በዩትዩብ ደረጃ የተወሰኑ ምስሎችን ማየት ችለናል፡፡ የቡድኑን ሙሉ ምልከታ ባይሰጠንም የተወሰነ ነገር ማየት ችለናል፡፡”
አሰልጣኙ ቡድናቸው በማዲቦ ኬይታ ስታዲየም ለሚያደርገው ጨዋታ ጥንቃቄን እንሚያስቀድም ይናገራሉ፡፡ “እግርኳስ ማለት መጀመሪያ መከላከል መቻል ነው፡፡ በመከላከል ሂደት ውስጥ ማጥቃት አለ፡፡ መጀመሪያ እራስህን ከፍተህ አትጫወትም የመጀመሪያ ጨዋታችን በነሱ ሜዳ መሆኑ በጥንቃቄ እንድንጫወት ያደርገናል፡፡ ይህ የመጨረሻ ዕድላችን ስለሆነ ከሜዳችን ውጪ በምናደርገው ጨዋታ ሙሉ ጥንቃቄ እያደረግን በሂደት ውስጥ ባሉን ፈጣን አጥቂዎች በመልሶ ማጥቃት ተጫውተን ውጤታማ ለመሆን ሰርተናል፡፡” ሲሉ አሰልጣኝ አጥናፉ ሃሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡