የወጣቶች እግርኳስ| 07-01-2009
ቀይ ቀበሮዎቹ በአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ የመጨረሻ ዙር ማጣሪያ ጨዋታ ነገ ማሊን ይገጥማሉ፡፡
ግብፅን ጥሎ ባለፈው ብሄራዊ ቡድን ውስጥ የነበሩት አጥቂው ጫላ ተሺታ፣ አምበሉ ማቲያስ ወልደአረጋዊ እና የመሃል ተከላካዩ ሳሙኤል ተስፋዬ በጨዋታው ዙርያ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
“ማሊን አክብደን አናየውም” ጫላ ተሺታ
ስለዝግጅት
“ዝግጅት በጣም ጥሩ እና ደስ የሚል ነበር፡፡ ፈጣሪ ረድቶን ከግብፅ ጨዋታ ጀምሮ አብረን ቆይተናል፡፡ ከግብፅ ጨዋታ መልስ ዕረፍት ተሰጥቶን ነበር፡፡ ከዕረፍት መልስ ሃዋሳ ላይ ጠንካራ ዝግጅት አድርገናል፡፡ ዝግጅታችን በጣም ጥሩ ነው፡፡”
ስለተጋጣሚ ቡድን ማሊ
“ያሸነፍናት ግብፅ ከማሊ የምትተናነስ አይደለችም፡፡ አስቀድሞም ስለግብፅ ሲወራ አክብደውት ነበር፡፡ ብዙ ግዜ ችግራችን ራሳችንን የበታች አድርገን እና አሳምነን ወደ ሜዳ የምንገባው ነገር ነው፡፡ እኛም 11 እነሱም 11 ሆነን ነው ወደ ሜዳ የምንገባው፡፡ ጥሩ የሰራው ቡድን ነው የሚያሸንፈው፡፡ ያለን የቡድን መንፈስ በጣም ደስ ይላል ፤ ስለዚህም ማሊን አናቀለውም አናከብደውም ሜዳ ላይ ገብተን ስራችንን መስራት ነው አላማችን፡፡”
ግብ ስለማስቆጠር
“ከፈጣሪ ጋር ግብ አስቆጥራለው ብዬ አስባለው፡፡”
“አሁንም ጥሩ የቡድን መንፈስ ስላለን ውጤት እናመጣለን” ማቲያስ ወልደአረጋይ
ስለዝግጅት
“ዝግጅታችን በጣም ጥሩ ነበር፡፡ ሃዋሳ ነበር ስንዘጋጅ የነበረው፡፡ ዝግጅታችን በጣም ጥሩ ሁኔታ አድርገናል፡፡ የመጀመሪያ ጨዋታችንን አሸንፈናል፡፡ ከፈጣሪ ጋር የማሊውን ጨዋታ ለማሸነፍ ተዘጋጅተናል፡፡ ወደ ማዳጋስካሩ የአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ ወሳኝ ጨዋታ በመሆኑ ተዘጋጅተናል፡፡”
ስለቡድን መንፈስ
“የቡድኑ መንፈስ ላይ የተቀየረ ነገር የለም፡፡ ፍቅር አላቸው ሁሉም ተጫዋቾች ናቸው፡፡ አሁንም ጥሩ የቡድን መንፈስ ስላለን ውጤት እናመጣለን፡፡”
ስለጨዋታው
“ከግብፅ ጋር ጥሩ ስለነበርን አሸንፈናል፡፡ ይህም እግርኳስ ነው ስለዚህ እኛ ጥሩ ከሆንን የማናሸንፍበት ምክንያት የለም፡፡ ከፈጣሪ ጋር እናሸንፋለን፡፡”
ከጉዳት ማገገም
“አሁን ላይ ከጉዳቴ አገገምያለው፡፡ ሙሉ ለሙሉ ከነበረብኝ ጉዳት ድኛለው፡፡”
” ከመስመር ተከላካዮቹ ጋር በቅንጅት ሰርተን ማሊን ማቆም ዋነኛው አላማችን ነው” ሳሙኤል ተስፋዬ
ስለዝግጅት
“ዝግጅታችን በጣም ደስ ይል ነበር፡፡ አሰልጣኞቻችን በበቂ መልኩ ልንሰራ የሚገባንን ሁሉ ነገር በዝግጅታችን ወቅት ሰጥተውናል፡፡ ከሞላ ጎደል ዝግጅታችን በጣም ጥሩ ነበር፡፡
ስለማሊው ጨዋታ
“የማሊውን ጨዋታ አናከብደውም፡፡ ግብፅን ማሸነፍ በመቻላችን በራስ መተማመናችን ጨምሯል፡፡ ማሊም ከግብፅ ይበልጥ ይከብዳል የሚል አስተሳሰብ የለኝም፡፡ አሰልጣኛችን በሚያዘን መሰረት ሜዳ ላይ አሪፍ ተጫውትን ጥሩ ውጤት ይዘን ለመመለስ እንሞክራለን፡፡ ተከላካይ እንደመሆኔ በደንብ ተዘጋጅቻለው፡፡ እነሱ በመስመር አጨዋወት እንደሚያጠቁ መረጃዎችን አግኝተናል፡፡ ከመስመር ተከላካዮቹ ጋር በቅንጅት ሰርተን ማሊን ማቆም ዋነኛው አላማችን ነው፡፡”
ስለቡድኑ መንፈስ
“ያለው የቡድኑ መንፈስ እና ተነሳሽነት በጣም ጥሩ ነው፡፡ ሁሉም በአዕምሮ ረገድ ለጨዋታው በቂ ዝግጅት አድርጓል፡፡ አዳዲስ የመጡት ተጫዋቾችም በቂ ለሆነ ግዜ አብረውን ባይቆዩም ለመላመድ አልቸገረንም፡፡”