የሴቶች እግርኳስ | 08-01-2009
በዩጋንዳ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ያለው የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ሲደርስ ኬንያ እና ታንዛኒያ ተጋጣሚዎቻቸውን በማሸነፍ በፍፃሜው ተገናኝተዋል፡፡ ኬንያ ኢትዮጵያን 3-2 ስትረታ ታንዛኒያ አዘጋጇን ዩጋንዳን 4-1 ማሸነፍ ችላለች፡፡
7፡30 በንጅሩ ቴክኒካል ማዕከል በተደረገው የመጀመሪያ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ኬንያ ኢትዮጵያን 3-2 ማሸነፍ ችላለች፡፡ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊዋ ኬንያ በውድድሩ ላይ ግብ ሳታስተናግድ ብትቆይም የሉሲዎቹ የፊት አጥቂ የሎዛ አበራ ሁለት ግቦች ሪከርዱን ለውጦታል፡፡ ግብ በማግባት ቀዳሚ የነበረችው ኢትዮጵያ ስትሆን ሎዛ በድንቅ ሁኔታ በ37ኛው ደቂቃ ግብ ማስቆጠር ችላለች፡፡
ከዕረፍት መልስ ግብ ለማግኘት ተጭነው የተጫወቱት ሃራምቤ ስታርሌቶች አካታትለው ባስቆጠሯቸው ሶስት ግቦች 3-1 መምራት ችለዋል፡፡ የኔዲ ኦኮት አቲኖ ሁለት እና የካሮላይን ኦሞንዲ የግንባር በመግጨት ያስቆጠሩት ግቦች ኬንያን ወደ መሪነት ሲያመጣት ሎዛ በ82ኛው ደቂቃ ውጤቱን ወደ አንድ ማጥበብ የቻለችበትን ግብ ከመረብ አዋህዳለች፡፡
09:30 ላይ በሁለተኛው የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ታንዛኒያ እንደተጠበቀው ዩጋንዳን 4-1 በማሸነፍ ለፍፃሜ አልፋለች፡፡ ኪሊማንጃሮ ኩዊንስ በመባል የሚጠሩት ታንዛኒያዎች የጨዋታ የበላይነት በክረስትድ ክሬንሶች ላይ የነበራቸው ሲሆን በመጀመሪያው አጋማሽ በዳንኤል ዶኒሲያ፣ ኦማሪ ማዋናሃሚሲ እና አብደላ ስቱማኢ ያስቆጠሩት 3 ግቦች የዩጋንዳ ደጋፊዎች ተስፋ አስቆርጧል፡፡ ራሺድ አሻ በሁለተኛው አጋማሽ ውጤቱን 4-0 ስታደርገው በውድድሩ ለዩጋንዳ ድንቅ የግብ ማስቆጠር ብቃቷን እያሳየች የምትገኘው ሃሲፋ ናሱና የማስተዛዘኛ ግብ ማስቆጠር ችላለች፡፡ ኢትዮጵያዊቷ ረዳት ዳኛ ወይንሸት አበራ ጨዋታውን በረዳት ዳኛነት መርታለች፡፡
የፍፃሜ እና የደረጃ ጨዋታዎች በመጪው ማክሰኞ የሚደረጉ ሲሆን ኢትዮጵያ ለሶስተኝነት ዩጋንዳን ትገጥማለች፡፡ ኬንያ እና ታንዛኒያ በተጠባቂ የፍፃሜ ጨዋታ የሚገናኙ ይሆናሉ፡፡