ኡመድ ኡኩሪ ለኤንግ ኤል ሃርቢ የመጀመሪያ የሊግ ጨዋታውን አድርጓል

  ኢትዮጵያውያን በውጪ | 12-01-2009 

ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ በተጀመረው የግብፅ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ ምሽት ኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢ በኤስማኤሊ 1-0 በተሸነፈበት ጨዋታ ላይ ኢትዮጵያዊው አጥቂ ኡመድ ኡኩሪ ለአዲሱ ክለቡ ኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢ የመጀመሪያ ጨዋታውን አድርጓል፡፡

ኡመድ በውድድር ዘመኑ መጀመሪያ ሌላኛውን የግብፅ ክለብ ኢኤንፒፒአይን በስምምነት ለቆ የካይሮውን ክለብ የተቀላቀለ ሲሆን በምሽቱ ጨዋታ ሙሉ 90 ደቂቃ መጫወት ችሏል፡፡

በቀድሞ የግብፅ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሻውኪ ጋሪብ የሚመራው ኤንታግ ኤል ሃርቢ የውድድር ዘመኑ የመጀመሪው የሊግ ግጥሚያው የነበረ ሲሆን ኤስማኤሊ ይህ ሁለተኛ ጨዋታው ነው፡፡ በኤስማኤሊያ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ የባለሜዳዎቹን የድል ግብ የቀድሞ የፈርኦኖቹ አማካይ ሆስኒ አብዳራቦ በፍፁም ቅጣት ምት በ75ኛው ደቂቃ አስጥሯል፡፡ ኡመድ በጨዋታው ላይ በቀኝ መስመር አጥቂነት መሰለፍ ችሏል፡፡ ኡመድ በተለይ በጨዋታው መገባደጃ ላይ ከፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውጪ በአክሮባት የሞከረው ኳስ በተከላካዮች ተጨርፎ ወደ ውጪ ወጥቷል፡፡ የቀድሞው የመከላከያ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ አጥቂ ኡመድ በኤንታግ ኤል ሃርቢ በቂ የመሰለፍ ዕድል እንደሚሰጠው ይታመናል፡፡

በመጀመሪያው ሳምንት ጨዋታ የሽመልስ በቀለ ክለብ የሆነው ፔትሮጀት ዋዲ ደግላን በመሃመድ ሳሂን የ94ኛ ደቂቃ ግብ 1-0 ማሸነፍ ችሏል፡፡ ሽመልስ በጨዋታው ላይ አልተሰለፈም ነበር፡፡ ፔትሮጀት በሁለተኛው ሳምንት አርብ ኤል ዳክልያን ከሜዳው ውጪ ኤል ሾርታ ስታዲየም ላይ ይገጥማል፡፡ የፔትሮጀት ቆይታውን ለተጨማሪ ሁለት ዓመት ያራዘመው አማካዩ ሽመልስ በጨዋታው ላይ እንደሚሰለፍ ይጠበቃል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *