የወጣቶች እግርኳስ | 14-01-2009
የኢትዮዽያ ከ17 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን ከማሊ ጋር ለሚያደርገው የአፍሪካ ከ17 አመት በታች ዋንጫ የመጨረሻ ማጣሪያ ወሳኝ የመልስ ጨዋታ ዝግጅቱን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
ከባማኮ መልስ ማረፊያቸውን አንፋራሲስ ሆቴል ያደረጉት ቀይ ቀበሮዎቹ ለመልሱ ጨዋታ ዝግጅት ከጀመሩ አራተኛ ቀናቸውን አስቆጠረዋል፡፡ ዛሬ ረፋድ ላይም በአበበ በቂላ ስታድየም 20 ተጨዋቾችን በመያዝ ልምምዱን አከናዉኗል፡፡
በፈጣን እንቅስቃሴ ውስጥ የመጨረሻ ሳጥን ውስጥ በመግባት ጎል የማስቆጠር ልምምዶች የዛሬው መርሃ ግብር አካል ነበሩ፡፡
ከታዳጊ ብሄራዊ ቡድኑ ጋር በተያያዘ በማሊው የመጀመርያ ጨዋታ ላይ ጉዳት ያጋጠመው ተከላካዩ ሳሙኤል ዛሬ ቀለል ያለ ልምምድ ያደረገ ሲሆን የቡድኑ ቁልፍ ተጨዋች የሆነው የሐረር ሲቲው ሚኪያስ መኮንን በሁለት ቢጫ ምክንያት ከቡድኑ ውጪ መሆኑ በቡድኑ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እንዳያሳድር ተሰግቷል፡፡
በኢትዮዽያ እና በማሊ መካከል የሚደረገው የመልስ ጨዋታ እሁድ መስከረም 22 ቀን 2009 በ10:00 አዲስ አበባ ስታድየም ላይ የሚካሄድ ይሆናል፡፡ አዲስ አበባ ስታድየምን ለጨዋታው ዝግጁ ለማድረግ በዕረፍት ቀናት ጭምር በመሰራት ላይ እንደሆነ ለመመልከት ችለናል፡፡