የአፍሪካ እግርኳስ | 16-01-2009
የ2016 ኦሬንጅ ካፍ ኮንፌድሬሽን ካፕ የፍፃሜ ጨዋታ በምድብ አንድ ተደልድለው ነበሩትን የዲ.ሪ. ኮንጎውን ቲፒ ማዜምቤ እና አልጄሪያውን ኤምኦ ቤጃያን አገናኝቷል፡፡
የአምስት ጊዜ የአፍሪካ ቻምፒዮኑ ቲፒ ማዜምቤ የአምና የኮንፌድሬሽን ካፕ አሸናፊው ኤቷል ደ ሳህልን ከሜዳው ውጪ ሶስ ላይ ባስቆጠረው ግብ ሲያሸንፍ ከሰሜን አፍሪካ ክለቦች ጋር እርስበእርስ ሲጫወት የበላይነቱን እየያዘ የመጠው ኤምኦ ቤጃያ የሞሮኮ ሻምፒዮን የሆነውን ፉስ ራባትን ማሸነፍ ችሏል፡፡
ቲፒ ማዜምቤ ከ2013 በኃላ ለመጀመሪያ ግዜ በተካፈለበት የኮንፌድሬሽን ካፕ ላይ ለፍፃሜ መቅረብ ችሏል፡፡ ሉቡምባሺ ላይ በተደረገው የመልስ ጨዋታ ኤቷል እና ማዜምቤ ያለግብ አቻ ተለያይተዋል፡፡ ከአንድ ሳምንት በፊት ሶስ ላይ 1-1 ነበር ማዜምቤ እና ኤቷል የተለያዩት፡፡ የጨዋታ እና የግብ ሙከራ ብልጫ የነበራቸው ማዜምቤዎች ሲሆኑ በዛምቢያዊው ኢንተርናሽናል ሬንፎርድ ካላባ መሪነት በተደጋጋሚ የኤቷልን የተከላካይ መስመር ማጥቃት ችለዋል፡፡ የኤቷልን ወሳኝ ግብ የማግባት እድል በሁለተኛው ግማሽ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ብራዚሊያዊው ዲያጎ አኮስታ ከአልካሊ ባንጉራ የተሻገረለትን ኳስ ቢያገኝም የማዜምቤ ግብ ጠባቂ ሲልቪያን ጎቦሆሆ አምክኖበታል፡፡ ዲዮ ካንዳም ለባለሜዳዎቹ የማሸነፊያ ግብ ማድረግ የሚችልበትን እድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ የቱኒዚያዊው አንተርናሽናል ግብ ጠባቂ አይመን ማትሎቲ ብቃት ጨዋታው ያለግብ አቻ እንዲጠናቀቅ ቢያደርግም ለፍፃሜ ለማለፍ ግን በቂ አልነበረም፡፡
ኤምኦ ቤጃያ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈበት የኮንፌድሬሽን ካፕ ለዋንጫ የተገመተውን ፉስ ራባትን በማሸነፍ አልፏል፡፡ ፉስ ራባት ከስድስት ዓመት በፈት ያሳካውን ዋንጫ ዳግም የማግኘት እድሉ ተበላሽቷል፡፡
ቤጃያ እና ፉስ ከሳምንት በፊት በቤጃያ ከተማ ያለግብ አቻ የተለያዩ ሲሆን በኮምፕሌክስ ስፖርቲፍ ሞላይ አል ሃሰን በተደረገው ጨዋታ ፉስ ራባት በመሃመድ ናሂሪ የ73ኛ ደቂቃ ግብ መሪ መሆን ችሎ ነበር፡፡ ተከላካዩ ናሂሪ ከማዕዘን የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ነበር ፉስን መሪ ያደረገው፡፡ በ90ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር የተመታውን ቅጣት ምት ከግብ በቅርብ ርቀት ያገነው ፋውዚ ራሃል ቤጃያን ወደ ፍፃሜ ያሳለፈች ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡ የእግርኳስ ህይወቱን በሙሉ በቤጃያ ያሳለፈው ራሃል በክለቡ ታሪክ ወሳኟን ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡ በምድብ ጨዋታዎች እና በግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች ሶስት ግብ ብቻ ያስተናገደው የቤጃያ የተከላካይ መስመር አሁንም በጥንካሬው ዘልቋል፡፡
ቲፒ ማዜምቤ በ2013 በኮንፌድሬሽን ካፕ ፍፃሜ በቱኒዚያው ሴፋክሲያን ተሸንፎ ዋንጫ ሲያጣ በ2015 ቻምፒየንስ ሊግ የአልጄሪያውን ዩኤስኤም አልጀርን አሸንፎ ዋንጫ ማንሳት ችሏል፡፡ በዲ.ሪ. ኮንጎ ከገዢው ፓርቲ ጋር ባላቸው ቅራኔ ምክንያት ባለቤቱ ሞይስ ካቱምቢ ከሃገራቸው የተሰደዱበት ክለቡ የተደበላለቀ የውድድር ዘመን በቻምፒየን ሊጉ እና ኮንፌድሬሽን ካፕ አሳልፏል፡፡
ኤምኦ ቤጃያ ከፍፃሜ ተጋጣሚው ማዜምቤ እጅግ ያነሰ ታሪክ በአፍሪካ እግርኳስ የክለቦች ውድድር ላይ አለው፡፡ በ2013 ወደ አልጄሪያ ሞቢሊስ ሊግ 1 ያደገው ክለቡ በሶስት ዓመታት ውስጥ ለኮንፌድሬሽን ካፕ ማለፍ ችሏል፡፡ ክለቡ በ2015 የአልጄሪያ ዋንጫን ማሸነፍ ችሏል፡፡ አልጄሪያዊው የቤጃያ አሰልጣኝ ናስር ሳንድዛክ በ2001 ሌላኛው የአልጄሪያ ክለብ ጄሲ ካቢሌን የካፍ ካፕ ቻምፒዮን አድርገዋል፡፡
ቤጃያ እና ማዜምቤ በምድብ አንድ በተገናኙበት ጨዋታ ቤጃያ ላይ 0-0 ሲለያዩ ሉቡምባሺ ላይ ማዜምቤ 1-0 ማሸነፍ ችሏል፡፡
ውጤቶች፡
ቲፒ ማዜምቤ (ዲ.ሪ. ኮንጎ) 0-0 ኤቷል ስፖርቲቭ ደ ሳህል(ቱኒዚያ) (1-1)
ፉት ዩኒየን ስፖርት (ሞሮኮ) 1-1 ሞሊዲያ ኦሎምፒክ ቤጃያ (አልጄሪያ) (1-1)